ለውጡን የምንደግፈው በማናቸውም ባህሪው ዛሬ ትናንትን እንዳይደግም ነው! በጀርመን የኢትዮጵያውያን የውይይትና የትብብር መድረክ

በጀርመን የኢትዮጵያውያን የውይይትና የትብብር መድረክ… በአሁኑ ጊዜ በአጠቃላይ በአገራችን እየተካሄደ ካለው ነባራዊ ሁኔታ በመነሳት፤ ሀ/ ለውጡ፤ የገጠመውና እየታዩ ያሉት መሬት ላይ ያሉ ችግሮች ምንድናቸዉ? በቲቪ እስክሪን (መስኮት)    በለውጥ አራማጁ አካል የሚነገረውና እየሆነ ያለው ሆድና ጀርባ የመሆን ችግር ለምን ይታዩበታል? ለ/ ማናቸውም ዓይነት ችግር ያጋጥም፤  ወቅቱ ሌላ አማራጭ እንደሌለም ስለሚያሳይ፤ ችግሩን ተቋቁሞ     ለውጡ የታሰበለትን ዓላማ  ግብ እንዲመታ የእኛ ድርሻ ምን መሆን አለበት?

በሚሉትና በአጠቃላይም ጠቅላይ ሚኒስትር  ዶ/ር አቢይ አሕመድ ወደ ስልጣን ከመጡበት ጊዜ አንስቶ አገራችን ኢትዮጵያ ውስጥ እየተካሄዱ ባሉት የለውጥ እርምጃዎች  ዙሪያ ተወያይቶና በለውጥ ሂደትም ያጋጠሙ ችግሮችን ገምግሞ ከዚህ የሚከተለውን የአቋም መግለጫ አውጥቷል። ከመግለጫዉ ባሻገርም ለውጡ የታለመለትን ግብ እንዲመታ መድረካችን የበኩሉን አገራዊ ግዴታ ከመወጣት ወደኋላ ላለማለትም እንደገና ቃል በመግባት ጭምር ነዉ።

ሁሉም እንደሚገነዘበዉ አገራችን ኢትዮጵያ ውስጥ ተንሰራፍቶ የነበረውን ጨቋኝና ጎሰኛ አገዛዝ ለመለወጥ ሃያ ሰባት ዓመታትን ያስቆጠረ መራራ ትግል ተካሄዶ አገዛዙ መግዛት ከማይችልበት ደረጃ ሲደርስ ተገዶም ቢሆን የአመራር ለውጥ እንዳደረገ ይታወቃል። በዚህ የስልጣን ሽግሽግ መንበረ ስልጣኑን በተረከቡት በዶ/ር አቢይ አሕመድ የሚመራው የለውጥ አራማጅ ኃይል የመሠረታዊ  ለውጥ ጥያቄዎችን ባይመልስም ከዚያ ባልተናነሰ መልኩ በርካታ ለአገርና ለወገን የሚጠቅሙ አስደናቂ ማሻሻያ ለውጦችን በማድረግ ለአለፈው አንድ ዓመት የሕዝባችንን ቀልብ ስቦ ቆይቷል። በታሪካችንም በዶ/ር አቢይ እንደሚመራዉ መንግሥት በአጭር ጊዜ ውስጥ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገር ሕዝባዊ ድጋፍ ያገኘ መንግሥት ነበረ ብሎ ለመናገር ያስቸግራል። ያም በመሆኑ ተቀማጭነቱን ፍራንክፈርት ከተማ ያደረገው … በጀርመን የኢትዮጵያውያን የውይይትና የትብብር መድረክም…. በዶ/ር አቢይ አሕመድ  ለሚመራው የለውጥ አካል ጁላይ 21/2018 ፍራንክፈርት ላይ ቁጥሩ በርካታ የሆነ ሰው  ለመጀመሪያ ጊዜ ኤርትራውያን  ወገኖቻችንን  ጨምሮ  በአደባባዮችና በዋና ዋና አውራ ጎዳናዎች ገንፍሎ በመውጣት ለተጀመረው ለውጥ  በሰላማዊ ሰልፍ ድጋፉን ገልጿል።  ከዚያም በተጨማሪ ኦክቶበር 31/2018 ዶ/ር አቢይ አሕመድ የአዉሮፓ ጉብኝት ወቅት አስተናጋጇ ከተማ ፍራንክፈርት ስለነበረች  የትብብር መድረኩ ከሃያ ሰባት ዓመት በኋላ  እንቁላልና ቲማቲም ከመወርወር በመታቀብ ለመጀመሪያ  ጊዜ ከኤምባሲዉ ጋር ጎን ለጎን በመተባበር የእሳቸዉ  የአዉሮፓ ጉብኝት እንዲሳካ በማድረግ  የእራሱን የማይናቅ ሚና ተጫውቷል።

እንደማንኛውም የአገሩን ጉዳይ እንደሚከታተል ዜጋ አገራችን ውስጥ እየተካሄ ያለውን ነውጥም ሆነ ለውጥ፣ ሽግግርም ሆነ ሽግሽግ በንቃት ስንከታተል ቆይተናል። ባለፈው አንድ ዓመትም በዶ/ር አቢይ አመራር በርካታ ተስፋ ሰጪና አበረታች የለውጥ ቱሩፋቶች መገኘታቸውን ሳንጠቅስ አናልፈም። ለአብነት ያህል፣

 • የተቃዋሚ ሃይሎች ወደ አገር ቤት እንዲመለሱና በአገሪቱ የፖለቲካ ሕይወት ገንቢ ሚና እንዲጫወቱ ጥሪ መደረጉ፣
 • የታሰሩ የፖለቲካ እስረኞች፣ ጋዜጠኞችና የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች መፈታታቸው፣
 • ሃሳብን በነጻ ማንሽራሽር መቻሉና በርካታ የሚዲያ ተቋማት መስፋፋታቸው፣
 • ነፃና ገለልተኛ የሆኑ እንደምርጫ ቦርድና ከፍተኛው የፍትሕ አካላት የመሳሰሉ ተቋማት በአዲስ መልክ መዋቀራቸው፣
 • በሁሉም አካባቢዎች ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት መሆኑን እንደተጠበቀ ሆኖ፣ በሰብአዊ መብት ጥሰትና የሀገር ሀብት ምዝበራ የተጠረጠሩ ባለስልጣናት ለፍርድ ለማቅረብ እየተደረገ ያለው ጥረት፣
 • ምስራቅ አፍሪካን የሰላም ቀጠና ለማድረግ ከጎረበት አገሮች ጋር የተጀመረውን በሰላም፣ በእኩልነትና በመግባባት ላይ የተመሰረተ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶች እንደስኬት ከምናያቸው አወንታዊ ጎኖች ሆነው አግኝተናቸዋል።

በዚያው መጠን ባለፈው ዓመት የተጀመረውን ተስፋ ሰጪ የለውጥ ሂደት ጥላሸት የሚያለብሱ የሚያሸማቅቁና የሚያሳፍሩ ድርጊቶች ተከስተው እጅግ አሳዝነውናል። ለምሳሌ ለመጥቀስ፣ 

 • በመንግስት ቸልተኝነትና ዳተኝነት የዜጎች ሰላምና ደህንነት ዋስትና አጥቶ ሽብር፣ ማስፈራራትና ዘረፋ ብሄራዊ ስጋቶች መሆናቸው፣
 • በጎሳ ጥላቻ ላይ የተመሰረተ መፈናቀል ከዚያም ጋር በተያያዝ በህግ የበላይነት በማስከበር ሽፋን ዜጎችን ከመኖሪያ ቀያቸው መፈናቀላቸው፣
 • በሚያሳዝን መልኩ ለሃሳብ በነጻ መንሽራሸር የለውጡ የጀርባ አጥንቶች ይሆናሉ ብለን የጠበቅናቸው የሚዲያ ተቋማት የሚዲያ ባለሃብቶቹ የዘር ክንድን በመንተራስ የጥላቻና የውሽት ፕሮፓጋንዳ ማስፋፊያ መሆናቸው፣
 • የፌዴራል መንግስት የፀጥታ አስከባሪ አካላት በክልሎች ጉዳይ ጣልቃ አንገባም በሚል ሰበብ ሕገ መንግስታዊ ግዴታቸውን ለመወጣት አለመቻላቸው፣
 • ከእንደዚህ ዓይነቶቹ የመንግሥት ቸልተኝነት ምክንያቶች በመነሳትም፤ ሰዎች እንደፈለጉ የሰውን ልጅ ዘቅዝቆ ከመስቀል ብቻ ሳይቆጠቡ፤ የሰዎችን ሕይወት በማጥፋት እስከነ መኪናቸው ማቃጠል መድረሳቸዉ፤
 • በአጠቃላይ በጎሳ የተከፋፈለን ሕብረተሰብ በኢትዮጵያዊነት አጀንዳ ሥር ማሰባሰብ፤ በፌዴራል አወቃቀርና በሕገ መንግሥቱ ላይ የጋራ አቋም መገንባት አለመቻል፣ የጎሳ ድርጅቶች እየተጠናከሩ የሕብረ ብሔራዊ ድርጅቶች  ደግሞ እየተዳከሙ እንዲመጡ እየተደረገ መሆኑ፣  

በኢትዮጵያዊነት፣ በአገር ግንባታና በሕገ  መንግሥቱ ላይ የጋራ ግንዛቤ መገንባት ከሁሉም ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ  መሆኑን በማመንና ዶ/ር አቢይ አሕመድ የጀመሩት ለውጥ በምንም ዓይነት መበረዝ ወይም መቀልበስ የሌለበት መሆኑን በመረዳት የለውጥ ኃይሉ ፈር ሲስት እየገሰጹ፣ እያረሙና እያስተካከሉ ውጤታማ እንዲሆን ከመታገል ውጭ በአሁኑ ጊዜ አገሪቱ ከምትገኝበት ነባራዊ ሁኔታ በመነሳት፣ ሌላ የተሻለ አማራጭ የሌለን መሆኑን በመረዳት የሚከተሉትን ጥሪዎች ለመንግሥት  እናቀርባለን፣

 • ለተፈናቀሉ ዜጎች አስችኳይ ሰብአዊ እርዳታና መልሶ ማቋቋም ከማድረግ ባለፈ መንግስት በዘለቄታው ማንኛውም

ዓይነት የዜጎች መፈናቀል እንዳይካሄድ እንዲቆጣጠር፣ በዚህ ረገድ እየታየ ያለው ችግር ሰው ሰራሽ የፖለቲካ ድርቅ ገብቶ እንጅ በተፈጥሮ ችግር ሕዝባችን እየተፈናቀለ አለመሆኑ የአደባባይ ምስጢር ስለሆነ ወገን በገዛ ወገኑ የመፈናቀል ትራጄዲ በአስቸኩዋይ መፍትሔ እንዲያገኝ፤

 • በየአካባቢው ለሚነሱት ጎሳ ተኮር አለመግባባቶች፣ ውዝግቦች፣ አስተዳደራዊ ችግሮችና የዜጎች ጥያቄዎች መንግስት በአስቸኳይ ፍትሀዊና ሕጋዊ መፍትሔ እንዲሰጥ፣
 • የህግ የበላይነትን የማስከበሩ ተግባር የመንግሥት ዋነኛ ሥራ ሆኖ ዜጎች በሥራ ላይ ያሉትን ሕጎች የማክበር ግዴታ እንዳለባቸው የማስገንዘብና ሀገር የስርዓተ አልበኞች መፈንጫ እንዳትሆን እንዲከላከል፣
 • አንድ መንግሥት ጠንካራነቱ ከሚለካባቸዉ ተግባራት አንዱ መንግሥታዊ መዋቅሩ ከፌዴራል እስከ ዞን ወረዳዎችና ቀበሌዎች ተንቀሳቅሶ የዜጎቹን መሠረታዊ መብት ማስከበር መቻሉና ከሁሉም በላይ ደግሞ በአገሪቱ ሠላም እንዲሰፍን የማድረግ አቅም ሲኖረው ነው። ከዚህ አጠቃላይ እውነታ ስንነሳ በዚህ ረገድ ባለፈው አንድ ዓመት የጎሉ ስህተቶች እየታዩ ናቸዉ። መንግሥት አስቀድሞ በዜጎች ላይ ጥቃት እንዳይደርስ መከላከል ሲገባው ንብረት ከወደመ፤ ሕይወት ከጠፋ በኋላ እንደ መልካም ጎረቤት ልቅሶ ሲደርስና መፅናናትን ሲመኝ ይስተዋላል። ከመንግሥት የሚጠበቀው የሕግ የበላይነትን በማስከበር የዜጎቹን ሕይወት ከሁሉም የጥቃት ዓይነቶች መታደግ ነውና በዚህ ረገድ ለሚታዩ ችግሮች አፋጣኝ መንግሥታዊ መፍትሔ ሊፈልግላቸው ይገባል እንላለን።
 • የመደበኛና የሶሻል ሚዲያዎች ሀላፊነት በተሞላበት፣ በነጻነትና አድልዎ በሌለው መንገድ ስራቸውን ማከናወናቸው መከታተል፣ ሕዝብን ከሕዝብ ከሚያጣላና ከሚያራብሽ ዘገባዎች እንዲቆጠቡ አስፈላጊውን እርምጃ እንዲወስድ፣
 • አዲስ አበባ የአፍረካ መዲና የኢትዮጵያ ዋና ከተማ ናት። ከዚህ ቀደም ከተማውንና ሕዝቡን ከፍፍሎ ለመግዛት ታስቦ በሕገ መንግስት ውስጥ የተካተቱ ከተማዋን የሚመለከቱ አከራካሪ አንቀፆች ተሻሽለው አዲስ አባበችን የሕዝባችን የሰላም፣ የብልፅግናና የእኩልነት መሀከል እንድትሆን መንግስት አስፈላጊውን ጥረት እንዲያደረግ እየጠየቅን በተለይ የአዲስ አበባ ሕዝብ ሕገ መንግስታዊ የመደራጀት መብቱን ተጠቅሞ በሰላማዊ መንገድ በመደራጀት እራሱን ከተለያዩ ጥቃቶች ለመከላከልና መብቱን ለማስከበር የሚያደርጋቸውን ሰላማዊ እንቅስቃሴዎች ሙሉ በሙሉ የምንደግፍ መሆኑን እንገልፃለን።

አገራችን በተለያዩ ችግሮች በተወጠረችበት በአሁኑ ወቅት የሚዲያ አውታሮች ዘርንና ቋንቋን በመያዝ በሚያሰራጩዋቸው ዜናዎችም ሆነ በሚያስተላልፏቸው መልዕክቶች ብርቱ አገራዊ ጥንቃቄ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፣ ከምንጊዜውም በላይ የሙያ ብቃታቸውን በሙያዊ ስነምግባር ታግዘው በታላቅ አገራዊ ሀላፊነትና የተጠያቂነት መንፈስ ሊሰሩ ይገባቸዋል። የጥላቻ ፖለቲካ ከሃሳብ በነጻ መግለጽ ጋር የማይገናኝ ወንጀል በመሆኑ፣ መንግስት በተለይ ሶሻል ሚዲያ ውስጥ ተደብቀው ጥላቻን የሚሰብኩ አገር አፋራሾች ላይ በአገር አቀፍም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ የመከላከልና የመከታተል ዘመቻ እንዲያደርግ እናሳስባለን።

የተፎካካሪ ፓርቲዎች ሁኔታ ስጋታቸውና ጭንቀታቸው ከራሳቸው ሕልውና ባለፈ ስለ አገሪቱና ሕዝቡ ጥያቄዎች ሲወያዩ አይታዩም፡፡ በውይይትና ድርድር ተግባብተው፣ በአንድ አገራዊ ራዕይ ስር ተሰባስበው ጠንካራ ድርጅቶች ከመመሥረት ይልቅ ትርፍ አልባ በሆነ ፉክክር ውስጥ ሲዳክሩ ይስተዋላል፡፡ በተናጠልም ወደ ክልሎⶭ የመድረስ አቅማቸው፣ በከፊል በኢህአዴግ

መዋቅሮች ጫና፣ በከፊል ደግሞ እኛ ክልል አትድረሱ በሚሉ አክራሪ ብሔርተኞች ምክንያት በጣም የተወሰነ መሆኑ በግልፅ እየታዩ ነው፡፡አንዳንዶቹ ፓርቲዎች በኢህአዴግ መንግሥት የታቀፉ በሚመስል ደረጃ በአገሪቷና በሕዝቦቿ ችግሮች ዙሪያ ዝምታን መርጠዋል፣ ያብቻ ሳይሆን መሪ ፕሮግራም ቀርፀው ማህበረሰቡን ማደራጀት አልቻሉም፡፡ በአንጻሩ በጎሳ ስም የተደራጁ ፓርቲዎች በየክልሉ እራሳቸውን በተሻለ መንገድ እያደራጁና ደጋፊዎች እያሰባሰቡ ያሉበትን ሁኔታ እየታዘብን ነው፡፡ ይሄም ለውጡ ወዴት እየሄደ ነው? የሚለውን ጥያቄ እንድናነሳ ያስገድደናል።

ለውጡን የምንደግፈው በማናቸውም ባህሪው ዛሬ የትናንቱ የሰቆቃ ዘመን ስህተት ተደግሞ ወገናችን እንዲፈናቀል፣ የዘረኞች የጥቃት ሰለባ፣ ስደተኛና ለማኝ እንዲሆን አይደለም። በንግግር ደረጃ በቴሌቪዥን መስኮት በተደጋጋሚ ሲነገር የምንሰማው ዴሞክራሲም አየር ላይ ተንጠልጥሎ እንዲቀር ሳይሆን፤ ወደ መሬት ወርዶ በሕይወት እንድንኖረው፤ ባጭሩ በአገራችን ምድር የሕግ የበላይነት ተክብሮ እና ሰላም ሰፍኖ ሕዝባችን ያለ ምንም ሥጋት በአገሩ ተዘዋውሮና ሰርቶ መኖር እንዲችል ሲደረግ እንደሆነ መድረካችን ያምናል። ከዚህ አጠቃላይ ግንዛቤ በመነሳት ለውጡ ሀዲዱን ስቶ ሙሉ በሙሉ ወደ ነውጥነት ሳይቀየር ሁላችንም በቅን አገራዊ ስሜት ያሉትን አማራጮች ሁሉ በመጠቀም ኢትዮጵያን ከገጠማት አደጋ ተረባርበን እንድንታደግ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን። 

ለውጡን የምንደግፈው በማናቸውም ባህሪው ዛሬ ትናንትን እንዳይደግም ነው! ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!
በጀርመን የኢትዮጵያውያን የውይይትና የትብብር መድረክ
Address: Postfach 111423, 60049 Frankfurt am Main
Email:
ethiopianforumfordialogue@gmail.com

Tel. Nr.: +4915773912794 +491782844931