ሐዋሳ ምን እየሆነ ነው ያለው? (ከትዝብቱ አየለ ዳኘው)

9940b162-8c6f-436d-9f5d-c9ed7ef2c739

የሃዋሳ ከተማን ለመጀመሪያ ጊዜ ያየኋት ከዛሬ 18 ዓመት በፊት በ1993 ዓ.ም ለአጭር ግዜ ነበር፡፡ ከተማዋ አሁን ባለችበት ደረጃ ባይሆንም ውብና ከፍተኛ የሆነ የዕድገት ተስፋ እንዳላት ያስታውቅ ነበር፡፡ ውበቷ የሚመነጨው ከመልክዓ-ምድራዊ አቀማመጧ፣ በምዕራባዊው የከተማዋ ጫፍ ተንተርሷት ከተኛው የፍቅር ሐይቋና በህዝብ አሰፋፈር ካላት ህብረ-ብሄራዊነት ነው፡፡ በ1996 ዓ.ም የከፍተኛ ትምህርት ዕድል ሳገኝ ከሃዋሳ ውጪ ለመማር ለአፍታም አላሰብኩም፤ ምክንያቱም በፍቅሯ ለመውደቅ ከ3 አመት በፊት የነበረኝ አጭር ቆይታ በቂዬ ነበር፡፡ በ1996 ዓ.ም ከተማው የዕድገት ፍንጭ የሚታይባት ከመሆኗ ባሻገር አልፎ አልፎ ውር ውር ከሚሉ ታክሲዎች በስተቀር እንደሌሎቹ የአገራችን ታዳጊ ከተሞች የፈረስ ጋሪ መነሃሪያ ነበረች፡፡ እነዚህ አሁን መንፈስን ለማደስ ለእግር ጉዞ የሚመኟቸው ውብ መንገዶቿ፣ የመዝናኛ ቦታዎቿና ውብ ህንጻዎቿ የእዚያን ግዜ አልታሰቡም ነበር፡፡ ይሁን እንጂ የህዝቦቿ መፈቃቀርና መከባባር ግን እንደወትሮው ጌጦቿ ነበሩ፡፡

የ1997ቱ ታሪካዊ አገራዊ ምርጫ ሂደት በአብዛኛው የተከታተልኩት በዚህች ውብ ከተማ ነበር፡፡ በሌላው የአገራችን አካባቢዎች እንደተስተዋለው የከተማዋ ህዝብም የምርጫውን ሂደት በአንክሮ ሲከታተልና የሚገባውን ተሳትፎ ሲያደርግ ነበር፡፡ ታሪካዊው ቀን በደረሰ ወቅትም ይበጀኛል ያለውን ተወዳዳሪ በመምረጥ ታሪክ አስመዝግቧል፡፡

ከዚህ ታሪካዊ ቀን በኋላ ግን ህይወት በአዋሳ የወትሮ ውበቷን ይዛ መቀጠል አልቻለችም፡፡ የወትሮው በህዝቦች መካከል የነበረው የእኩልነትና አስደማሚ ግንኙነት ልብ-ወለድ በሆነው የወያኔና ዉሉደ-ወያኔዎች የልዩነት ትርክት ምክንያት በሚያሳዝን ሁኔታ እንዲበላሽ ተደረገ፡፡ በከተማዋ በአብዛኛው የምርጫ ጣቢያዎች ቅንጅት በከፍተኛ ድምጽ ማሸነፉ ለወያኔና የጽልመት ተከታዮቹ የሚዋጥ አልነበረም፡፡ በመሆኑም ምርጫውን ተከትሎ በሕወሐት ትዕዛዝ የክልሉ ካድሬ ተሰብሶቦ በከተማዋ የቅንጅት ማሸነፍ ከመጤው(ይህ ቃል እጅግ አሳዛኝ ነገር ግን በወያኔ የከፋፍለህ ግዛ ሥርዓት በዘር ግንድ የአካባቢው ተወላጅ ላልሆኑ ኢትዮጵያውያን የሚሰጥ ስያሜ ነው) ሕዝብ መብዛት ጋር በግድ እንዲያያዝ ተደረገ፡፡ በመሆኑም የከተማው አሰፋፈርና ስፋት መለወጥ እንዳለበት ድምዳሜ ላይ ተደርሶ በአስቸኳይ እንዲተገበር አቅጣጫ ተቀመጠ (በዚህ ላይ የመለስ ዜናዊ ቀጥተኛ ጣልቃ ገብነት እንደነበረበት ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ሰዎች ሲናገሩ ይደመጣሉ)፡፡ በዚህም መሰረት ፈቃደኛ የሆኑ የሲዳማ ማህበረሰብ አባለት ከገጠርና በአካባቢው ካሉ ትናንሽ ከተሞች ተመልምለው ሁለት ሁለት ቦታ በከተማው እንዲሰጣቸው ተደርጎ የከተማው የህዝብ አሰፋፈር እንዲቀየር ለማድረግ ተሞከረ፡፡ ከስፋት አንጻር በተቀመጠውም አቅጣጫ ከተማዋን እስከ 10 ኪ.ሜ በመለጠጥ በዙሪያዋ ያሉ የገጠር አካባቢዎች የከተማዋ አካል እንዲሆኑ ተደረገ፡፡ ይህ ሁሉ ድካም እንግዲህ ህዝብን በውለታ አስሮ በቀጣይ ምርጫዎች ድምጽ ለማግኘት ነበር፡፡ ይህንን ተከትሎ የሚከተሉት ኩነቶች በከተማዋ መታየት ጀመሩ፡-

1. በሰፈራ መልክ ወደ ከተማዋ እንዲገቡ የተደረጉ የሲዳማ ተወላጆች አብዛኞቹ የዘራፊ ካድሬዎች ሰለባ በመሆን የተሰጣቸውን መሬት በርካሽ ዋጋ እየሸጡ እንዲወጡ ተደረገ፡፡ በዚህም ምክንያት የከተማዋ መሬት በጥቂት በወያኔ የሚደገፉ የሲዳማ ካድሬዎች እጅ ወደቀ፡፡ እነዚህ ካድሬዎች በአቋራጭ ወደ ሃብት ማማ ተወነጨፉ፤ ጎን ለጎንም ለሕወሐት ታማኝ መሆናቸውን በሃብታቸው ምለው አረጋገጡ፡፡
2. እነዚህ ጀሌ ካድሬዎች በመሬት ዘረፋ ከሚያጋብሱት መጠነ-ሰፊ ሃብት ባሻገር የሕወሐት ጥቅም አስከባሪ በመሆን ብቅ አሉ፡፡ በዚህም የሌላ ብሄር ተወላጆችን ከተማው የኛ ነው፣ ከፈለግን ልናባርራችሁ እንችላለን በማለት ነዋሪው አንገቱን ደፍቶ እንዲኖር አደረጉ፡፡ ከዚህም ባለፈ በከተማዋ የሚፈጠሩትን ማንኛውንም የንግድና የሥራ ዕድሎች ከወያኔ በሚደረግላቸው ልዩ ድጋፍ መቆጣጠር ቻሉ፡፡
3. እነዚህ ጀሌ ካድሬዎች ከሃብት ዘረፋውና ከማስፈራራቱ ባሻገር ወደ ገጠራማው የሲዳማ ህዝብ መኖሪያዎች በመንቀሳቀስ ሃዋሳ ከተማ የሲዳማ ህዝብ ብቻ እንደሆነችና ህዝቡ በአገኘው አጋጣሚ ሁሉ ይህንን እንዲያንጸባርቅ ሲጎተጉቱ ከረሙ (በተለይ የወላይታ ህዝብ ዋነኛ ደመኛቸው እንደሆነ ሰበኩ)፡፡ የህዝቡን የክልል ጥያቄም በእዚህ አፍራሽ እንቅስቃሴ እንዲቃኝ የሚቻላቸውን ሁሉ አደረጉ ፡፡
4. የከተማዋ ነዋሪ ከዕለት ወደ ዕለት የሚከናወነውን ሕገ-ወጥ እንቅስቃሴ ቢያውቅም በማን እንደሚደገፍ ስለገባውና አቤት ቢልም ለውጥ ሊመጣ እንደማይችል ስለተገነዘበ ቀን እስኪወጣ ድረስ አንገቱን ለመድፋት ተገደደ፡፡
5. በመለስ ዜናዊ ያሽነት የተተገበረው የአሰፋፈር ስልት በከተማዋ የህዝቦች መስተጋብር ላይ የሚታይ ለውጥ አስከተለ፡፡ በመሆኑም በአንጻራዊነት አዲስ ሰፈር ተብለው የሚታወቁት እንደ አቶቴ፣ በከፊል አላሙራ፣ አዲሱ ገበያ፣ አሊቶ፣ ጨፌ የመሳሰሉ የከተማዋ ሰፈሮች በአብዛኛው በሲዳማ ተወላጆች እንዲያዙ ተደረገ፡፡ በአንጻሩም የከተማዋ ነባር ሰፈሮች ከ1997 ዓ.ም በፊት በነበረው የስብጥር አሰፋፈር ቀጠሉ፡፡ ይህም በኢትዮጵያ ከሚገኙ ትላልቅ ከተሞች በተለየ ሁኔታ ከተማዋ ሰው ሰራሽ የሆነ የህዝብ አሰፋፈር እንዲኖራት ደረገ፡፡

የሴራው ውጤት

1. ጥቂት በወያኔ ጥላ ስር የተጠለሉ የሲዳማ ብሄር ካድሬዎችና ከእነሱ ጋር የተጎዳኙ ግለሰቦች የሃብት ማማ ላይ እንዲወጡ ተደረገ (እዚህ ላይ ልብ ሊባል የሚገባው በእዚህ ሴራ ውስጥ የሚሳተፉ የሌላ ብሄር ካድሬዎችና ደጋፊዎች ያሉ መሆናቸውን ነው)፡፡ በዚህም ለሕወሐት ውለታቸውን ለመክፈል የሌላ ብሄር ተወላጆችን በማስፈራራት አንገታቸውን እንዲደፉ ለማድረግ የሚቻላቸውን ሁሉ አደረጉ፡፡
2. በእነዚህ ወንጀለኛ ካድሬዎችና የጥቅም ተጋሪ ጥቂት የሲዳማ ተወላጆች ምክንያት ሌላው የከተማዋ ነዋሪ አጠቃላይ የሲዳማን ህዝብ በጥርጣሬ እንዲመለከት ተደረገ፡፡
3. እንዲተገበር የተደረገው አሰፋፈር በተለምዶ በከተሞች አካባቢ የሚኖረው ሁሉ አቀፍ የህዝቦች መስተጋብር እንዳይኖር በማድረጉ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱ እንደሌሎች ከተሞች አድጎ ውህደት በመፍጠር አንድ አይነት ማኅበረ-ኤኮኖሚያዊ ማኅበረሰብ እንዳይፈጠር አደረገ፡፡
4. ጀሌ ካድሬዎቹ በገጠሩ የሲዳማ ማኅበረሰብ ውስጥ ገብተው በዘሩት ክፉ ወሬ ምክንያት አንዳንድ ግለሰቦች በሚያሳዩት ያልተገባ ባህሪይ ምክንያት (ለምሳሌ የጫምባላላ በዓልን አክብረው ሲመለሱ በሆቴሎች ውስጥ በመግባት ከተመገቡ በኋላ ያለመክፈል ወዘተ) በዩኔስኮ የማይዳሰስ ቅርስነት ተመዝግቦ የአገራችን ኩራት የሆነውን የፍቼ ጫንባላላ ክብረ በዓል በሌላው ማኅበረሰብ ዘንድ በተሳሳተ መነጽር እንዲታይ ተደረገ፡፡ በመሆኑም በአካል በተገኘሁባቸው ያለፉት ሰባት አመታት ክብረ በዓሉ በከፍተኛ ውጥረት ሲከበር መታዘብ ችያለሁ፡፡በተለይ በ2004 ዓ.ም በተከበረው የፍቼ ጫምባላላ በዓል ወቅት ከተማዋ በከፍተኛ ጭንቅ ውስጥ ገብታ የነበረ ሲሆን የመለስ ዜናዊ ሞት ዜና ሁኔታው እንዲረግብ ማድረጉን ብዙዎች ያስታውሱታል፡፡  

በሰኔ ወር 2010 ዓ.ም የተከሰተው ብጥብጥ ቅጽበታዊ ምክንያት/Immediate cause/

ከላይ ለማሳየት የሞከርኩት የኩነት-ውጤት ግንኙነት ባለፈው ዓመት ለተከሰተው አሳዛኝ ብጥብጥ በአንድም በሌላም በኩል አስተዋጽዖ አድርጓል፡፡ ባሳለፍነው ዓመት እንደተለመደው የፍቼ ጫምባላላ በዓል በከፍተኛ ውጥረት እንዲከበር ለማድረግ ሁሌም የማይተኙት የወያኔ ጀሌ ካድሬዎች የአገሪቱን የፖለቲካ ለውጥ እንደ አሉታዊ ግብዓት በመጠቀም ውጥረቱን አንድ ደረጃ ለማሳደግ ሌት ተቀን ሲሰሩ ከረሙ፡፡ ይህ ተግባር በቀጥታ በሕወሐት የተደገፈ እንደነበር ጉዳዩን በቅርብ የሚከታተሉ የከተማዋ ነዋሪዎች የሚያውቁ ሲሆን በዋነኛ አስፈጻሚነት ብቅ ያሉት ግን የደኢሕዴን ህሊና ቢስ ከፍተኛ ካድሬዎች ነበሩ (እዚህ ላይ ሺፈራው ሽጉጤ ከፍተኛ ሚና እንደነበረው የሲዳማ ተወላጆች ሳይቀር በግልጽ ይናገራሉ)፡፡ ዋናው በዓል ከመከበሩ አንድ ቀን ቀደም ብሎ ማለትም ሰኔ 5 ቀን 2010 ዓ.ም እነዚህ ህሊና ቢስ ካድሬዎች አደራጅተው ያዘጋጇቸው ወጣቶች (አብዛኛዎቹ የጎዳና ተዳዳሪዎች ናቸው) የወላይታ ተወላጆች በብዛት በሚኖሩበትና በሚሰሩበት አሮጌ ገበያ አካባቢ በመንጋ እንዲሄዱ በማድረግ ብጥብጥ ኢንዲፈጥሩ ያደረጉ ሲሆን በዚህም በጥቂት ሰዎች ላይ ጉዳት እንዲደርስ ሆኗል፡፡ ይህንን አደገኛ አዝማሚያ የተገነዘቡ ህዝባዊ የክልሉ አመራሮች በሚቀጥለው ቀን በሚከበረው ዋና በዓል ላይ ሊከሰት የሚችለውን አደጋ በመገንዘብ የመከላከያ ሰራዊት እንዲገባ ያደረጉ ቢሆንም በወቅቱ የከተማው ከንቲባ የነበረውና በአሁኑ ወቅት ከችግሩ ጋር በተያያዘ ጉዳዩ በፍርድቤት እየታየ ያለው ግለሰብ በመገናኛ ብዙሃን ላይ ቀርቦ የችግሩን ግዝፈት በማንኳሰስ መግለጫ መስጠቱ ጉዳዩ በመንግስት በኩል ተገቢውን ትኩረት እንዳያገኝ ሆነ፡፡

ዋናው በዓል በሰፊው የሲዳማ ህዝብ ጨዋነትና በመከላከያ ሰራዊት ጥረት በሰላም የተጠናቀቀ ቢሆንም ለውሉደ-ወያኔ ካድሬዎቹ ግን ህልማቸው የከሸፈበት ያልጠበቁት አጋጣሚ ሆኖባቸው አለፈ፡፡ በመሆኑም በአንድ በኩል የጥፋት ዕቅዳቸውን በቀጣይ በምን መልኩ ማሳካት እንደሚችሉ ዕቅድ በማውጣት በሌላ በኩል ደግሞ ባልጠበቁት መንገድ ወደ ከተማዋ የገባውን የመከላከያ ሰራዊት ከከተማዋ በቶሎ እንዲወጣ አስተዳደራዊ ጫና ለማድረግ ሴራቸውን በማስፈጸም አብረው እየመከሩ ያሉትን አመራሮች ሲወተውቱ እንቅልፍ አጥተው አደሩ፡፡ ውትወታው በደጋፊዎቻቸው አመራሮች እገዛ ሰምሮላቸው መከላከያ ሰራዊቱ በዋናው በዓል ማግስት ማለትም ሰኔ 7 ቀን 2010 ዓ.ም ከከተማው እንዲወጣ ሆነ፡፡ ይህ አጋጣሚ የከተማውን አመራሮች ጨምሮ ሌሎች የክልሉ አመራሮች በተከሰተው አሳዛኝ አጋጣሚ ተባባሪ እንደነበሩ ግልጽ ማሳያ ሆኖ ሊጠቀስ ይችላል፡፡ እነዚህ ህሊና ቢስ ካድሬዎች የመከላከያ ሰራዊቱን መውጣት ካረጋገጡ በኋላ ቀድመው ባደራጇቸውና የከተማው ነዋሪ ባልሆኑ ወጣቶች የወላይታ ተወላጆችን፣ መኖሪያ ቤታቸውንና የንግድ ድርጅቶቻቸውን ለይተው መጠነ ሰፊ ጥቃት ማድረስ ጀመሩ፡፡ ሁኔታው በመጀመሪያ የከተማውን ነዋሪ ግራ ያጋባና ምን እተከናወነ እንደሆነ እንኳ ለመገመት ያስቸገረ የነበር ሲሆን በኋላ ግን የወጣት ቡድኖቹ ሲናገሩና ሲከውኑ ከነበረው ተግባር ዘር ተኮር ጥቃት እንደሆነ ለመገንዘብ ተቻለ፡፡ በከተማው የሚኖሩ የሲዳማ ተወላጆች እተደረገ በነበረው ድርጊት ክፉኛ በመቆጣት ወጣቶቹን ለመገሰጽ ከፍተኛ ጥረት ሲያደርጉ የነበረ ቢሆንም ከአቅማቸው በላይ በመሆኑ ሊሳካላቸው አልቻለም፡፡ በመሆኑም ፊታቸውን ጎረቤት ያሉ የወላይታ ወገኖቻቸውን ወደ ማትረፍ አዙረው የሚችሉትን ያክል በቤታቸው በመደበቅ ያልተቻላቸውን ደግሞ ከአካባቢው እንዲርቁ በማድረግ ሊደርስባቸው ከሚችለው አሳዛኝ አደጋ ታደጓቸው፡፡ ከዚያም አልፈው ንብረቶቻቸው እንዳይነካ በመከላከል ሁኔታው እስኪረጋጋ በማቆየት ኢትዮጵያዊ ወገንተኛነታቸውን አሳዩ፡፡

ቀደም ተብሎ እንደተጠቀሰው በወያኔና ውሉደ-ወያኔ ካድሬዎች ሴራ የከተማው ህዝብ አሰፋፈር እንዲዛባ በመደረጉእነዚህ ህገወጥ ወጣቶች ኢላማቸውን በቀላሉ እንዲያጠቁ ጥሩ መደላድል ፈጥሮላቸዋል፡፡ በሌላ በኩል ዘር ተኮር ጥቃት በአዲሱ ገበያ፣ በአሊቶና ከፊል አላሙራ በሚባሉት የከተማዋ አካባቢዎች መወሰዱን የሰሙ የወላይታ ተወላጆች በበኩላቸው በብዛት በሚኖሩበት 01 እና 02 ቀበሌዎች አጸፋዊ ጥቃት በመሰንዘር ንጹሃን የሲዳማ ተወላጆች እንዲጎዱ አድርገዋል፡፡ ሁኔታው ይህንን በመሰለ አደገኛ ሁኔታ ላይ በደረሰበት ደረጃ እንኳን የከተማውም ሆነ የክልሉ አስተዳደር በራሱ ጸጥታ አስከባሪዎችም ሆነ የመከላከያ ሰራዊትን ትብብር በመጠየቅ ለመቆጣጠር ያደረጉት ምንም አይነት ጥረት አለመኖሩ የከተማው ነዋሪዎችን በእጅጉ አሳዝኖ አልፏል፡፡ ይህ የከተማውና የክልሉ አስተዳደር ዝምታ የልብ ልብ የሰጣቸው ህገወጦች ሰኔ 7 2010 ዓ.ም ማምሻውን መከላከያ እስኪገባ ድረስ ከተማዋን የጦርነት ቀጣና አድርገዋት ዋሉ፡፡ በውጤቱም ጥቂት የማይባሉ ንጹሃን በአሰቃቂ ሁኔታ ህይወታቸው ተቀጠፈ፣ በርካታዎቹ ከባድና ቀላል የመቁሰል አደጋ ደረሰባቸው እንዲሁም በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ከቤታቸው ተፈናቀሉ፡፡ በንብረት ላይ ሲደርስ የነበረው ጥቃት በጭፍን ስለነበር ክሊኒኮች ሳይቀር የውድመቱ ሰለባ ሆነው ማየት እጅግ አሳዛኝ ክስተት ነበር፡፡ ጥቃቱ በሌሎች እንደ ይርጋለም፣ ለኩ፣ ወንዶ ገነት፣ ሻመና የመሳሰሉ ከተሞች የተደረገ ሲሆን በተለይ ከክስተቱ በኋላ እኔ በአካል የተመለከትኩት ለኩ በሚባለው ከተማ የደረሰው ውድመት እጅግ አሳዛኝ ነበር፡፡

በሌላ በኩል ሃዋሳ ላይ ዘር ተኮር ጥቃት እየተፈጸመ መሆኑን የሰሙ የወላይታ ሶዶ ከተማ ነዋሪዎች ኩነቱን ለማውገዝ የተቃውሞ ሰልፍ እንዲፈቀድላቸው ለከተማውና ለዞኑ አስተዳደር በተደጋጋሚ ጠይቀው መከልከላቸውን ተከትሎ አርብ ሰኔ 8 ቀን 2010 ዓ.ም በቁጣ አደባባይ መውጣታቸውንተገን በማድረግ የእነዚሁ ወያኔ ካድሬ ተላላኪዎች በሰው ህይወትና በንብረት ላይ ከፍተኛ የሆነ ውድመት አደረሱ (ወያኔና ተባባሪዎቹ እንደተመኙት በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ መምታት ቻሉ)፡፡ በተለይ የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲና የግብርና ቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ኮሌጁ የደረሰባቸው ውድመት እጅግ ከፍተኛ ሊባል የሚችል ነበር፡፡ ለወላይታ ሶዶው ውድመት የዞኑ መስተዳደርና የከተማው አስተዳደር ኃላፊነቱን መውሰድ እንደሚገባቸው ብዙዎች ያምናሉ፡፡ ምክንያቱም የሃዋሳው ክስተት ትኩሳት በወላይታ ዞን ወረዳዎች ላይ ሊከሰት እንደሚችል አይደለም እነዚህ አካላት ማንኛውም ለአቅመ-ማሰብ የደረሰ ሰው መረዳት የሚችለው ነበር፡፡ በመሆኑም ትክክለኛ የህዝብ ወገን ቢሆኑ ኖሮ የጸጥታ ኃይል ትብብርን በመጠየቅ የተቃውሞ ሰልፉን ፈቅደው ህዝቡ ቁጣውን በሰላማዊ ሁኔታ ገልጾ እንዲመለስ ማድረግ ይችሉ ነበር፡፡ ይልቁንም እነዚህ አመራሮች የዞኑን አስተዳዳሪ ጨምሮ ራሳቸውን ከህዝቡ ቁጣ ለማትረፍ ሲሯሯጡ መታየታቸው በወቅቱ ሲገለጽ ነበር፡፡ በወቅቱም በከተማው የደረሰው አጠቃላይ የንብረት ውድመት እስከ 150 ሚሊየን ብር እንደሚገመት በመገናኛ ብዙኃን ተገልጧል፡፡

የድሕረ-ብጥብጥ ኩነቶች/Post violence events or the aftermath/

1. የስጋት ደመና

ቀደም ብዬ ከላይ ለመጠቆም እንደሞከርኩት ከታሪካዊው የ1997 ዓ.ም ምርጫ በኋላ ከኢትዮጵያዊነቱ ውጪ ሌላ የማያውቀው ሰፊው የከተማዋ ነዋሪ ጥርስ ተነክሶበት በስጋት እንዲኖር የተደረገ ቢሆንም ሲታዘባቸው የቆየው አፍራሽ ተግባራት ይህንን መሰል ውጤት ይዘው ይመጣሉ የሚል ግምት በፍጹም አልነበረውም፡፡ በመሆኑም በሰኔ ወር 2010 ዓ.ም በከተማዋ የተመለከተው ኩነት ከአዕምሮው በላይ ሆኖበት ለማመን ከመቸገሩም በላይ የመንፈስ መረጋጋቱ ተገፎ ድንጉጥ ለመሆን ተገዷል፡፡ በከተማዋ ካሉ የሲዳማና ወላይታ አክራሪ ብሄርተኞች በአካል ከሚሰማቸውና በማህበራዊ ድረ-ገጾች ከሚናፈሱት ወሬዎች በመነሳት ብጥብጡ ተመለሶ ሊከሰት ይችላል የሚል ስጋት ውስጥ በመውደቁና የክልሉም ሆነ የፌድራል መንግስቱ ለከተማዋ ሰላም መረጋገጥ እምብዛም እየጣሩ ባለመሆኑ መሸሻ ያጣ ምስኪን ሆኗል፡፡

2. የከተማዋ የኤኮኖሚ እንቅስቃሴ መቀነስ

የተከሰተውን ብጥብጥ ተከትሎ የከተማዋ ገጽታ በከፍተኛ ደረጃ በመጉደፉ በፍጥነት ወደላይ እየተወነጨፈች የነበረችው ውብ ከተማ በአጭር ጊዜ ውስጥ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዋ ወርዷል፡፡ የከተማዋ ውበት ስቧቸው መዋዕለ-ንዋይ ለማፍሰስ ወደ ከተማዋ የመጡ ባለሃብቶች ወደመጡበት እንዲመለሱ የተገደዱ ሲሆን በሳምንቱ መጨረሻ ከተለያየ የአገራችን አካባቢዎች (በተለይ ከአዲስ አበባ) ወደከተማዋ የሚጎርፈው ህዝብ በከፍተኛ ደረጃ በማሽቆልቆሉ የከተማው የንግድ እንቅስቃሴ ቀንሷል፡፡  የከተማዋ ነዋሪ ሳይቀር በከተማዋ ላይ መዋዕለ-ንዋዩን ለማፍሰስ ሁለቴ እንዲያስብ ተገዷል፡፡ በውጤቱም ለብዙ የከተማዋና አካባቢ ነዋሪ የስራ ዕድል ፈጥረው የቆዩት ተቋማት እንቅስቃሴ በመቀነሳቸው የስራ አጥ ቁጥር እንዲጨምር አስተዋጽዖ እያደረገ ይገኛል፡፡ በከተማዋ የሚገኙ የመንግስትም ሆነ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ለተለያዩ ጉዳዮች የሚያደርጉትን ስብሰባዎች ከከተማዋ ውጪ ለማድረግ የተገደዱ በመሆኑ ከተማዋ ከመሰል ኩነቶች የምታገኘው ገቢ እንዲቀንስ ሆኗል፡፡

3. ኤጄቶ የተባለው ቡድን ውልደትና እንቅስቃሴ  

አክቲቪስት ጃዋር መሐመድ ወደከተማዋ ብቅ ብሎ እስኪመለስ ድረስ ስለ ኤጄቶ ሰምቶ የሚያውቅ ያለ መሆኑን እጠራጠራለሁ፡፡ ይህ ኤጄቶ የተባለው ቡድን ለሲዳማ ክልል መመስረት እታገላለሁ የሚል  በአብዛኛው በብሄረሰቡ ወጣቶች የተመሰረተ ቡድን ሲሆን በሚያደርጋቸው አዎንታዊና አሉታዊ እንቅስቃሴዎች ታዋቂነትን እያገኘ የመጣ ቡድን ነው፡፡ ቡድኑ በዋነኝነት በጃዋር መሃመድ የሚደገፍ እንደሆነ በብዙዎች ዘንድ የሚታመን ሲሆን የደቡብ ክልል ፕሬዚደንቱም የዚህ ቡድን ህቡዕ ደጋፊ እንደሆኑ ይገመታል፡፡ ይህ ቡድን በተከታታይ ባደረጋቸው እንቅስቃሴዎች የሲዳማ ዞን አመራሮችና ካድሬዎች ላይ መፍጠር በቻለው ተጽዕኖ ተዳፍኖ የቆየውን የሲዳማ ህዝብ በክልል የመደራጀት ጥያቄ ወደፊት እንዲመጣ ማድረግ የቻለ ሲሆን ጉዳዩንም የደቡብ ክልል ምክርቤት አጽድቆ ለህዝበ ውሳኔ ለምርጫ ቦርድ እንዲያስተላልፈው ጉልህ ሚና ተጫውቷል፡፡ ቡድኑ የክልል ጥያቄው ቶሎ መፍትሄ እንዲያገኝም ከስራ ማቆም አድማ ጀምሮ እስከ ጾታን መሰረት ያደረገ ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግን የመሳሰሉ  ማስገደጃ ተግባራትን ላለፉት ወራቶች ሲፈጽም ቆይቷል፡፡ በተከታታይ የተካሄዱትን ሁለት ሰላማዊ ሰልፎች ፍጹም ሰላማዊ በሆነ መንገድ ማከናወኑ ከፍተኛ ሙገሳን ያሰጠውን ያክል የስራ ማቆም አድማውን ለማሳካት የሄደበት መንገድ ግን የከተማዋን ነዋሪ ተጨማሪ ስጋት ውስጥ እንዲገባ ያደረገ ነበር፡፡ ከእነዚህ በይፋ ከተደረጉት እንቅስቃሴዎች በተጨማሪ በቡድኑ ስም የሚንቀሳቀሱ ወጣቶች በውሃ ቀጠነ ምክንያት ትምህርት ቤቶችን ሲያውኩ፣ የንግድ ቤቶችን ለማዘጋት ወይም ለመዝረፍ ጥረት ሲያደርጉና በአጠቃላይ የከተማው ነዋሪን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ሲያውኩ የተስተዋሉበት በርካታ አጋጣሚዎች ነበሩ፡፡ በተለይ የቡድኑ መሪዎች የነበሩ ወጣቶች በመኪና አደጋ ህይወታቸው ማለፉን ተከትሎ በቀብራቸው ዕለት የተሞከረው የከተማዋን የትምህርትና የንግድ እንቅስቃሴ የማወክ ተግባር፣ በተጨማሪም በከተማዋ የሚገኙትን ማናቸውንም ተቋማት የማስታወቂያ ሰሌዳ በሲዳምኛ እንዲቀየሩ በሚል የተደረገው ሃይል የቀላቀለ ዘመቻ ነዋሪውን ከፍተኛ ስጋት ውስጥ እንዲወድቅ አድርጎት ነበር፡፡ በርግጥ ኤጄቶ ከጊዜ ወደጊዜ የትግሉን መንገድ ሰላማዊ በሆነ ሁኔታ ለማከናወን በመወሰኑ ይመስላል ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ጥያቄውን ሰላማዊና በተደራጀ መንገድ ሲያቀርብ የተስተዋለ ሲሆን በቡድኑ ስምም ተጠቅመው የተለያዩ ህገ ወጥ ተግባራት የሚፈጽሙ ወጣቶችን ሲያወግዝ እተስተዋለ ይገኛል፡፡ በአጠቃላይ በእንቅርት ላይ ጆሮ ገድፍ እንዲሉ ኤጄቶ እንቅስቃሴ በከተማዋ ገጽታ ላይ አሉታዊ አሻራ እያሳረፈ በመምጣቱ ወደ ከተማዋ ይመጣ የነበረውን ከፍተኛ ገቢ በእጅጉ ጎድቶታል፡፡

4. በክልሉም ሆነ በፌድራሉ መንግስት ላይ ተስፋ መቁረጥ

ከሰኔ 2010 ዓ.ም ጀምሮ በከተማዋ የሰፈነውን ህገ ወጥ ድርጊት ለመከላከል የክልሉም ሆነ የፌድራሉ መንግስት የሳዩት ቸልተኝነት በከተማዋ ነዋሪ ዘንድ ከፍተኛ ተስፋ መቁረጥን አስከትሏል፡፡ ብዙዎች ባለፉት 12 ወራት እንደታዘቡት በከተማዋ መንግስት ህግን ለማስከበር ያደረገው እንቅስቃሴ በጣም ደካማ ነበር፡፡ በመሆኑም አንዳንድ የከተማዋ ነዋሪዎች ቢያንስ ቤተሰባቸውን ከከተማዋ ለማራቅ በመወሰን እተንቀሳቀሱ ሲሆን በዚህም ሳቢያ የንግድና መኖሪያ ቤቶች ሽያጭ ዋጋ ከዚህ ቀደም ከሚታወቀው በእጅጉ ወርዷል፡፡  

የከተማዋ ቀጣይ ዕጣ ፋንታ

ከላይ እንደተጠቀሰው ከተማዋ ከሰኔ 2010ሩ ብጥብጥ ቆፈን እስካሁን ድረስ ያልተላቀቀች ሲሆን አሁን ከፍተኛ ጡዘት ላይ ያለው የሲዳማ ክልል ጥያቄ ማዕከል መሆኗ ለከተማው ህዝብ ዕጣ ፈንታዋ አሳሳቢ ሆኖበት ይገኛል፡፡ በተለይ የኤጄቶ እንቅስቃሴ እየተጠናከረ መጥቶ ሃምሌ 11 ቀን 2011 ዓ.ም ክልል ለማወጅ በከፍተኛ ዝግጅት ላይ መገኘቱን በመጥቀስ በተለያዩ የማህበራዊ ድረ ገጾች እንዲሁም በተግባር የነባሩን ክልል መስሪያቤቶች ስም እስከመቀየር የሄደበት አግባብ የከተማዋን ነዋሪ ተጨማሪ ስጋት ውስጥ እንዲወድቅ አድርጎታል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የቡድን ዝርፊያዎችና ድብደባዎች መበራከት፣ የክልል ጥያቄውን የሚጻረሩ ንግግሮችን በሚያደረጉ ነዋሪዎች ላይ የሚፈጸመው ዛቻና የቡድን ጥቃት እንዲሁም በሞተር ሳይክል በቡድን በሚንቀሳቀሱ ወጣቶች በምግብና መጠጥ ቤቶች ላይ የሚፈጸመው ሁከት እየተባባሰ መምጣትና የክልል ጥያቄው በሰላማዊ መንገድ የማይፈታ ከሆነ እንደ አማራጭ በኤጄቶ የተያዘውን የሃይል እንቅስቃሴ ለማስፈጸም ከተለያዩ የሲዳማ ዞን አካባቢዎች ተመልምለው በአንዳንድ የብሄረሰቡ ባለሃብቶች ድጋፍ ወደከተማዋ እንዲገቡ የተደረጉ ወጣቶች ተግባራት የከተማዋ መጻዒ ዕድል አስከፊ ሊሆን እንደሚችል አመላካች ተደርገው ሊወሰዱ ይችላሉ፡፡  

በአጠቃላይ ከላይ ከተጠቀሱት ኩነቶች በተጨማሪ የኤጄቶ የሲዳማ ክልልነት ጥያቄ እንደጠበቀው አመርቂ መልስ በመንግስት በኩል እየተሰጠው ባለመሆኑ በቡድኑ አባላት ዘንድ ከፍተኛ ቅሬታን ፈጥሯል፡፡ ይህንንም ተከትሎ የሲዳማ ክልልነትን ለማወጅ ቡድኑ ለሃምሌ 11 ቀን 2011 ዓ.ም የያዘው ቀጠሮ ምን ይዞ ሊመጣ እንደሚችል ለመገመት አስቸጋሪ ሆኗል፡፡ በዚህ ዙሪያም የክልሉም ሆነ የፌድራል መንግስት ዝምታ የበለጠ አስጨናቂ ጉዳይ ነው፡፡ በአገራችን ከተሞክሮ ማየት እንደሚቻለውና በተግባር በቡድኑ አባላት ላይ ከሚታየው ተስፋ መቁረጥ የክልል ጥያቄው የማይሳካ ከሆነ በከተማዋና ሌሎች የዞኑ አካባቢዎች ተቃውሞ አዘል የሃይል እንቅስቃሴዎች ሊከናወኑ እንደሚችሉ መገመት ይቻላል፡፡ ይህ ደግሞ የብዙ ሰላማዊ ነዋሪዎችን ህይወትና ንብረት አደጋ ላይ ሊጥል ይችላል፡፡ ስለሆነም ከዚህ ቀደም በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች እንደታየው ሳይሆን መንግስት አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት በማድረግ በከተማዋ እየታዩ ያሉት እንቅስቃሴዎች በሰላማዊ ሁኔታ መፍትሔ እንዲያገኙ ማድረግ ካልሆነ ደግሞ ዜጎቹን ከማንኛውም አይነት ጥቃት እንዲከላከል ንደ አንድ ሰላማዊ የከተማዋ ነዋሪ ጥሪዬን አቀርባለሁ፡፡

ፈጣሪ ለአገራችን ሰላምን፣ ለህዝባችን ደግሞ አንድነትን ያድልልን፡፡

አሜን!