የሲዳማ ጥያቄ እና የደቡብ ኢትዮጵያ ፖለቲካ (በቦጋለ ታከለ)

0

የሲዳማ ዞንን ወደ ክልልነት ለማሳደግ እታገላላሁ የሚለው የሲዳማ ልሂቃን ጥያቄ ውስጠ ሚስጥሩ ሲገለጥ የደቡብ ህዝቦች ሁሉ ተባብረው ያቀኗትን ውቧን የአዋሳ ተማን ለሲዳማ ብቻ የማድረግ አምሮት ነው፡፡ይህ አምሮት የኢትዮጵያ ህዝቦች ሁሉ ተባብረው ያሳመሯትን አዲስ አበባን የኦሮሚያ ንብረት ለማድረግ በሚቋምጡ የኦሮሞ ብሄርተኛ ቢጤዎቻቸው ይደገፋል፡፡

የኦሮሞ ልሂን የሲዳማ ፖለቲከኞችን የክልል አምሮት አጥብቀው የሚደግፉበት ዋነኛው ምክንያት እነሱ እንደሚሉት የሲዳማ ህዝብ እና የኦሮሞ ህዝብ በሲአን እና በኦነግ በኩል ተቃቅፈው ሲታገሉ ስለኖሩ አይደለም፡፡የኦሮሞ ህዝብ እና የሲዳማ ህዝብ እንደማንኛውም ማህበረሰብ የጠብም የፍቅርም ታሪክ ያላቸው ህዝቦች እንደሆኑ አሰበ ረጋሳ …በሚልርዕስ የሰራው ጥናት ያመለክታል፡፡እንደ ጥናቱ ከሆነ የኦሮሞ ህዝብ በአመዛኙ ሰላማዊ ግንኙነት ያለው ከጌዲኦ ህዝብ ጋር ሲሆን ከሲዳማ ጎረቤቱ ጋር ጦር መማዘዙ የበዛ ታሪክእንዳለው ነው፡፡

ከታሪክ አለፍ ብለን የቅርቡን ዘመን መስተጋብር ብናይ ደግሞ የሲዳማ እና የኦሮሞ ፖለቲከኞች ወንዶ ገነት በተባለችው ለምለም ወረዳ ላይ ያላቸው ረዥም ጊዜ የወሰደ ቁርቁስ ጋብ ያለው የአቶ መለስ ኢህአዴግ አካሄድኩት ባለው ሪፈረንደም ነው፡፡ ሪፈረንደሙ በሲዳማ ክልል ከሚገኘው ለሙ የወንዶገነት ወረዳ ግዛት ውስጥ የተወሰነውን ለኦሮሚያ ክልል ጀባ ብሏል፡፡እነዚህ ለኦሮሚያ ክልል የተሰጡ ግዛቶች የጆግራፊ አቀማመጥ በመሃል ሲዳማ ዞን ውስጥ እንደ ደሴት የተበጣጠሱ የኦሮሚያ ቀበሌዎችን የፈጠረ ነው፡፡ እዚህ ስምምነት ላይ ለመድረስ በአቶ ሽፈራው ሽጉጤ የሚመራው የሲዳማ እና አባዱላ በሚመሩት የኦሮሞ ፖለቲከኞች መሃከል የሰውን ህይወት ጭምር ያስከፈለ ትልቅ ቁርቁስ ነበረ፡፡

ከዚህ እውነታ ባፈነገጠ መልኩ አሁን አሁን የኦሮሞ እና የሲዳማ ህዝቦች በፍቅር ብቻ የኖሩ አስመስሎ የመተረኩ ነገር እየበረከተ መጥቷል፡፡ ይህ ተረክ ከኦዴፓ ጋር ተዋሃድኩ ያለው የቀድሞው ኦዴግ አመራሮችን (ዶ/ር ዲማ ነገዎን) እና የኦነግ አመራሮችን አዋሳ አብርሮ አምጥቶ የኤጄቶ እና የቄሮ ህብረት በሚል ስብሰባ ላይ አስቀምጦ ነበር፡፡ በዚህ ስብሰባ ላይ እውነቱ እየተጋነነ አንዳንዴ የሌለውም እየተፈጠረ የሲዳማ እና የኦሮሞ ህዝቦች ትግል የመንትዮች ትግል እንደሆነ ተወርቷል፡፡እነ ዶ/ር ዲማ ነገዎን ከመሰሉ ከጉምቱ የኦሮሞ ብሄርተኞች እስከ ጃዋር እና ፀጋየ አራርሳን የመሰሉ ዱላ ተቀባዮቻቸው ድረስ የኦሮሞ ብሄርተኞች የሲዳማን ክልል በማዋለድ በኩል ከሲዳማ ፖለቲከኞች ጎን ቆመናል ባዮች ናቸው፣አማካሪም ሆነው ታይተዋል፣እንደ ትግል ስትራቴጅስትም ሲቃጣቸው ይስተዋላል፡፡ የኦሮሞ ብሄርተኞች በዚህ ልክ ለሲዳማ ክልልነትእውን መሆን ቆመን እንደር የማለታቸውን ምስጢር መመርመር አስፈላጊ ነው፡፡

ምክንያት አንድ

የመጀመሪያው ምስጢር የአዋሳ እና የአዲስ አበባ ጥያቄ ተመሳስሎሽ ነው፡፡ አዋሳን የግሉ ለማድረግ የሚሰግረው የሲዳማ ልሂቃን ምኞት አዲስ አበባን የራሱ ለማድረግ ከሚንገላታው የኦሮሞ ልሂቃን ፍላጎት ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡የኦሮሞ ልሂቃን አዲስ አበባ የኦሮሞ ተፈጥሯዊ ርስት ነች እንደሚሉት ሁሉ የሲዳማ ልሂቃንም አዋሳ ለሲዳማ ህዝብ እንደዛው ነች ይላሉ፡፡ሆኖም አዲስ አበባ ዓለም አቀፍ ከተማ ከመሆኗ እና በህገመንግስቱም የራሷአስተዳደር ያላት እንጅ በኦሮሚያ ግዛት ስር አለመሆኗ ግልፅ በሆነ ሁኔታ በመደንገጉ የኦሮሞ ልሂቃን አዲስ አበባን የራሳቸው የማድረግ ምኞታቸው ዕለቱን ሊሆን የማይችል፣አስቸጋሪ እና ውስብስብ ሆኖታይቷቸዋል፡፡በዚህ ላይ አዲስ አበባን የእኔ የሚያስብላቸው ከባድ ፍቅር አዲስ አበባን የጋራ መዲናው አድርጎ ከሚያስበው መላው ኢትዮጵያዊ ጋር ሁሉ የሚያላትማቸው፣ባለጋራቸውን የሚያበዛባቸው ብርቱ ጉዳይ ሆኗል፡፡

ስለዚህ በተባበረ ክንድ የለሙ ከተሞች በስተመጨረሻው በአቅራቢያቸው ባለ አንድ ብሄር በባለቤትነት ሊጠቀለሉ እንደሚችሉ በአዋሳ በማስመድ(እንደ “political pilot test” በመውሰድ) ቀጥሎ ወደ አዲስ አበባ መምጣት የኦሮሞ ልሂቃን ጥበብ ቢጤ አካሄድ ነው በሲዳማ ክልል ናፋቂ ፖለቲከኞች ዙሪያ የሚያዞራቸው፡፡ ባይሆን ኖሮ የኦሮሞ ልሂቃን የወላይታ፣ከንባታ፣ሃድያ፣ጋሞ፣ጎፋ፣ከፋ፣ጉራጌ ወዘተ ክልል ጠያቂዎችምን ለሲዳማ ክልል ጠያቂዎች በሚያደርጉት መጠን ሲያበረታቱ መታየት ነበረባቸው፡፡

ምክንያት ሁለት

ደቡብ ኢትዮጵያ የኦሮሞ ብሄርተኞች ዘወትር በሚረግሙት እና ዛሬ እንደተደረገ ሁሉ በሚንገሸገሹበት የአፄ ምኒልክ መስፋት ወደ ኢትዮጵያ የተጨመረ ግዛት ነው፡፡ ቢሆንም የደቡብ ኢትዮጵያ ምሁራን አፄ ምኒልክን በመርገሙም ሆነ ኢትዮጵያ ለምትባል ሃገር ህልውና ምንግዴ በመሆን ከኦሮሞ ልሂቃን ጎን የሚቆሙ አይደሉም፡፡በአንፃሩ የኦሮሞ ልሂቃን የደቡብ ምሁራን የተበድየ ፖለቲካቸው እየየ እድርተኛ እንዲሆኗቸው አጥብቀውይሻሉ፡፡ከደቡብ ኢትዮጵያ ምድር የዘውግ ማንነቱን አስቀድሞ ኢትዮጵያዊነቱን ሁለተኛ አድርጎ ደረት የሚደቃ የተበድየ ፖለቲካው አልቃሽ ምሁርም ሆነ ፖለቲከኛ የማግኘቱ ነገር ግን በመሻታቸው ልክ አልተሳካላቸውም፡፡ይህ የኦሮሞ ፖለቲከኞችን ብግን የሚያደርጋቸው ሃቅ ነው፡፡ከዚህ ብስጭታቸው ተንፈስ የሚያደርጋቸው፣የተበዳይ ማህበር የመስረቱን አምሮታቸውን ለማስታገስ ዘንበል የሚልላቸው የሲዳማ ክልል ጠያቂ ልሂቅ ነው፡፡የሲዳማ ልሂቃንም ቢሆኑ አዋሳ ከተማን ይዘን  ክልል እንሁን ይበሉ እንጅ የኦሮሞ ብሄር ፖለቲከኞች በሚፈልጉት ልክ ኢትዮጵያዊነታቸውን ጠሎች አይደሉም፡፡

የኦሮሞ ልሂቃን የደቡብ ምሁራንን እና ፖለቲከኞችን ኢትዮጵያዊ ማንነትን እና እንደባንዲራ ያሉ ሃገራዊ ምልክትን በመጥላቱ ረገድ እንደ እነሱ ለማድረግ የሚፋትሩት መፋተር ሲዳማ ልሂቃን በኩል በር ያገኘ መስሏል፡፡ይህ በር የኦሮሞ ልሂቃን በደቡብ ክልል ላይ ሲያዩት የሚጠሉትን ኢትዮጵያዊ ማንነትን የማጥበቅ ነገር የሚፈረካክሱበት ሁነኛ መግቢያ ነው፡፡የሲዳማ ልሂቃንን የክልልነት ጥያቄ ተከትሎ እየተግተለተለ ያለው ወደ አስር የሚጠጉ ዞኖች የክልልነት ጥያቄ አዲስ በሚመሰረቱ ክልሎች ትኩስ ብሄርተኝነትን የሚያመጣ እና የቀደመውን የደቡብ ልሂቃን የኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነት የሚፈታተን ነገር ነው፡፡ይህ ከኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነት ጋር ክፉ ጠብ ላላቸው የኦሮሞ ብሄርተኘነት ፖለቲከኞች ሰርግ እና መልስ ነው፡፡

የኦሮሞ ልሂቃ ለበርካታ አመታት ምኒልክን የመርገም ተረክ በመተረኩ ስልት ማግኘት ያልቻሉትን የደቡብ ልሂቃን የተበድየ ፖለቲካ አጋርነት በሲዳማ ልሂቃን በኩል ገብተው በሚያደርጉት እጅግ የረቀቀ የፖለቲካ ስራ በቀጥታ ሳይሆን በተዘዋዋሪ የደቡብ ኢትዮጵያ ልሂቃንን በሚፈልጉት (ኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነት ሁለተኛ አድርጎ በጎሳ ማንነት ላይ በማተኮሩ) መንገድ ለማስኬድ ይችላሉ፡፡

ምክንያት ሶስት

ከላይ በምክንያት ሁለት የተጠቀሰው የኦሮሞ ልሂቃን በደቡብ ክልል ፖለቲካ ውስጥ ያለ ፍላጎት ወደ ሶስተኛው እና የመጨሻው ምክንያት(ውጤትም ሊባል ይችላል) የሚያደርስ ነው፡፡ ይህ ሶስተኛው ምክንያት የደቡብ ኢትዮጵያ ልሂቃንን የቀደመ የኢትዮጵያ ብሄርተኝነት አስጥሎ በኩሽ ህብረት ጥላውስጥ የመውደቅ ፍላጎት የመተካት ስልት ነው፡፡ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለይ በተደጋጋሚ እየተቀነቀነ ያለው የኩሽ ህብረት ዝንባሌ የኦሮሞ ብሄርተኞች አጥብቀው የሚጠሉትንኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነት ከደቡብ ኢትዮጵያ ምድር ነቅለው እነርሱ በሚመሩት አዲስ ኩሻዊ ማንነት የመተካት እንቅስቃሴ ነው፡፡ይህ እንቅስቃሴ ዋነኛ አላማው በኦሮሞ ብሄርቶች ዘንድ የኢትዮጵያ ፈጣሪ የሚባለውን የአማራ ብሄር ማግለል ነው፡፡

ይህን ሲሉ ያልተረዷቸው ነጥቦች አሉ፡፡አንደኛው የዘውግ ፖለቲካው የክርስትና አባት የሆነው እና አማራውን በመጥላት እና በማግለሉ በኩል ዋነኛ አጋር የሆነው ህወሃት መራሹ የትግራይ ምድር በኩሽ ህብረት ውስጥ ሊገባ የማይችል ሴማዊ መሆኑ ነው፡፡በዋነኝነት አማራውን ለማግለል የተወጠነው የኩሽ ማንነት ከደቡብ ክልልም የጉራጌን እና የስልጤን ብሎም የኦሞቲክ ቋንቋ ተናጋሪ የሆነውን የወላይታ፣ዳዋሮ፣ጋሞ፣ጎፋ የመሳሰሉትን ህዝቦች የሚያገል ነው፡፡ግራም ነፈሰ ቀኝ ኩሽ ህብረት በደቡብ ኢትዮጵያ ስር የሰደደውን የኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነት ነቅሎ በሌላ ለመተካት ያለመ የኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነት ፈተና ነው፡፡ እውነት ማድረጊያው እና መግቢያው መንገድ ደግሞ የሲዳማ ልሂቃን የክልልነት ጥያቄ እንቅስቃሴሲሆን ፊት አውራሪዎቹም የሲዳማ እና የኦሮሞ ብሄርተኞች ናቸው፡፡

የሲዳማ ልሂቃን አካሄድ

አዋሳን ማዕከል ያደረገ የሲዳማ ክልላዊ መንግስት መመስረትን ብቻ አልመው የተነሱት የሲዳማ ፖለቲከኞች ከእዚህ ሁኔታ በቀር በምንም እንደማይስማሙ አበከረው ይናገራሉ፡፡የሲዳማ ክልልን ከመመስረት ፍላጎታቸው ይልቅ አዋሳን የግል የማድረግ እራስ ወዳድነት የበዛበት ፍላጎታቸው ዘለግ እንደሚል ባለፈው ፅሁፌ በደንብ አስረድቻለሁ፡፡ይህንኑ ፍላጎታቸውን ገቢራዊ ለማድረግ ይህንኑ ጥያቄያቸውን ሲያፍን የኖረው ህወሃት ከመንበር እስከሚታጣ ጠብቀዋል፡፡ህወሃት ከመሃል ወደ ዳር ሃገር መሄዱ እርግጥ ሲሆን የሲዳማ ፖለቲከኞች ኤጄቶ የሚባል የገጠር ጎረምሶች ቡድን አቋቁመው ገና እግሩን በደንብ ባልተከለውን የዶ/ር አብይ መንግስት ፋታ እንዲነሳ አድርገዋል፡፡የሚገርመው ነገር ይህ ኤጄቶ የሚባለው የሲዳማ ጎረምሶች ቡድን የኢትዮጵያ ህዝብ የህወሃትን የበላይነት ለመጣል ባደረው ትግል ወቅት ከነአካቴው ያልነበረ እና አንዳች አስተዋፅዖ ያላበረከተ መሆኑ ነው፡፡ኤጄቶ ለያዥ ገራዥ ያስቸገረ ደራሽ ታጋይ የሆነው ታጋዮችን እስርቤት አስገብቶ ቁምስቅል የሚያሳየው ህወሃት ሄዶ ሰው አላስርም ሲል ቃል የገባው የዶ/ር አብይ መንግስት መንበሩን ከያዘ፣ታጋይ የሚፈተንበት ዘመን ካለፈ በኋላ ነው፡፡

ይህን ቡድን በማደራጀት እና አይዞህ በማለት አቶ ሚሊዮን ማቲዎስን፣አቶ ቴድሮስ ገቢባን እና አቶ ደሴ ዳልኬን ጨምሮ በኢህአዴግ መራሹ መንግስት የስልጣን መሰላል ላይ ያሉ የሲዳማ ልሂቃን አስተዋፅኦ እንደነበረ ባለስልጣናቱ በየመገናኛ ብዙሃኑ ሚሰጡት ቃለምልልስም መረዳት ይቻላል፡፡ በተጨማሪ በአዋሳ ምድር ኤጄቶ በቀን በብርሃን ሲዳማ ያሆነን ሰው በድንጋይ ቀጥቅጦ ሲገድል፣ሲዘርፍ እና በከተማዋ ከሲዳምኛ በቀር በሌላ ቋንቋ የተፃፉ ታፔላዎችን እያወረደ ሲሰባብር ክልሉን የሚዘውሩት የሲዳማ ባለስልጣናት ዝም ብለው መመልከታቸው አቶ ቴድሮስ ገቢባ እንደውም አፋቸውን ሞልተው ወጣቶቹ ልክ ናቸው እስከማለት መድረሳቸው የኤጄቶ ውንብድናው የበዛ አካሄድ በሲዳማ የመንግስት ባለስልጣናት ጭምር እንደሚታገዝ አስረጅ ነው፡፡

ሌላው አስገራሚ ነገር ኤጄቶ የተባለው የሲዳማ የገጠር ጎረምሶች ቡድን ረብሻ ለማስነሳት ባሰበበት ቀን አዋሳ የሚገባ እንጅ አዋሳ የሚኖር አለመሆኑ ነው፡፡እነዚህ ከገጠራማ አካባቢዎች ገስግሰው መጥተው ውንብድና በተሞላበት አኳኋን የነዋሪውን ሰላም እያደፈረሱ፣ንግድ እና የመንግስት ስራ መስራት እስከሚያስቸግር ድረስ አዋሳ የእኛ ነች ሲሉ አዋሳ ተወልዶ ያደገው ወጣት ዝም ብሎ ከመመልከት በቀር የሚያደርገው ነገር የለም፡፡ የዚህ ምክንያቱ እዚህን ጎረምሶች ከገጠር የማመላለሻ ትራንስፖርት ወጭን ከመሸፈን ጀምሮ በከተማዋ ውስጥ ገብተው የሚያደርጉትን ህገወጥ ስራ አይቶ እንዳላየ በማለፉ በኩል  የመንግስት ባለስልጣናት ሚና በግልፅ የሚታይ በመሆኑ ነው፡፡ስለዚህ የከተማው ህዝብ ራሱን በመንግስት በኩል ህጋዊ ከለላ የሌለው አድርጎ ስለሚያስብ በዝምታ ማየትን መርጦ ኖሯል፡፡

ነገሩን ግልፅ ለማድረግ ራሴ በአይኔ ያየሁትን አጋጣሚ ባነሳ በአዋሳ ከተማ በወላይታ ዲቻ እና በአዋሳ ከነማ መሃከል የሚደረግ የእግር ኳስ ጨዋታ በሚስተናገድበት በአንዱ ቀን ከጨዋታው የሚመለሱ ኤጄቶዎች በመንገድ ላይ ያሉ ሱቆች በራቸው ላይ ያደረጉትን የሚሸጥ ነገር ሲያሻቸው በእግራቸው፣ሲፈልጉ በያዙት ዱላ እየመቱ ያልፋሉ፡፡በዚህ መሃል የወንዶች ልብስ መሸጫ ሱቅ ውስጥ አንድ አራት ሆነው በቡድን ገብተው ነጋዴው አሻንጉሊት ላይ የሰቀላቸውን ልብሶች ለማውለቅ ሲታገሉ ባለሱቁ የሞትሞቱን አላስወልቅም ብሎ ሲታገል ትርምስ ተፈጠረ፡፡

ትርምሱን ሊያስቆሙ የመጡ ፖሊሶች ሲዳምኛ እየተናገሩ ኤጄቶዎቹ በር እንዲለቁ አደረጉ፡፡ ከዛም ፖሊስ ተብየዎቹ የሰው ሱቅ ገብተው የሚበጠብጡ ኤጄቶዎችን ትተው ንብረቴን አላዘርፍም ብሎ ለብቻው ከአራት ጎረምሶች ጋር የሚታገለው ነጋዴ ላይ አንዱ በተለይ አይኑን አጉረጥርጦ መቆጣት ጀመረ፣እንደመማታት እየሞከረው ነጋዴው ቶሎ ሱቁን ዘግቶ ወደ ፖሊስ ጣቢያ እንዲሄድ ያዋክበው ጀመር፡፡ነጋዴው ግራ በመጋባት ደግሞ ጥፋተኛው እኔው ሆንኩኝ እያለ ሱቁን ዘግቶ ከተቆጣው ፖሊስ ፊት ፊት ሲሄድ የሰው ሱቅ ዘው ያሉት ጎረምሶች እየተሳሳቁ ተረኛ ተበጥባጭ ፍለጋ ወደፊት ቀጠሉ፡፡ይህ አንድ አጋጣሚ ነው፤አዋሳ በርካታ እንዲህ ያሉ በህግ አካላት ጭምር የሚታገዙ ውንብድናዎችን ታስተናግዳለች፡፡

በአንድ በኩል የገጠር ጎረምሶችን አደራጅተው የአዋሳ ከተማን በእጅ አዙር የሚያምሳምሱ የሲዳማ ልሂቃን እና ባለስልጣናት የሚሰሩት ህገ-ወጥ ስራ ይህ ብቻ አይደለም፡፡ የሲዳማ ክልልነት ጥያቄ በ11/11/11 በህግም ሆነ በጉልበት እንደሚያስፈፅሙ እርግጠኞች ስለነበሩ ከዛ ከሶስት ወራት በፊት ጀምሮ ሰላሳ ስምንት የሲዳማ ልሂቃንን የያዘ የሲዳማ ክልል አስተዳደር ሴክሬታሪያት የሚባል መዋቅር አወዋቅረዋል፡፡ እነዚህ ሰላሳ ስምንት ሰዎች ህዝብ የመረጣቸው አይደሉም፣የክልሉ መንግስትም አያውቃቸውም፣ እነ አቶ ሚሊዮን ግን በግል አያማክሯቸውም አይደፏቸውም ማለት አይደለም፡፡

ይህ ሰላሳ ስምንት ሰዎችን የያዘው ሴክሬታሪያት በመንግስት የማይታወቅ፣በህዝብም ያልተመረጠ ህገወጥ ቢሆንም በሶሻል ሚዲያዎች በሚለቀቁ ቪዲዮዎች ሲመሰረት እና ስብሰባውን ሲያካሂድ ታይቷል፡፡ ህገ-ወጡ ሴክሬታሪያት የሚሰራቸው ስራዎች የሲዳማን ክልል ህገመንግስት ረቂቂ እስከ ማዘጋጀት እንደሚሄድ ነው ሲዳማ እና ኤጀቶ ሲዳ አፌርስበሚለው የማህበራዊ ድህረገፆች በሚለቃቸው ተከታታይ ፅሁፎች እ የቪዲዮ ምስሎየሚገልፀው፡፡

ይህ ሴክሬታሪያት ኤጀቶ የተባለው ፅንፈኛ ቡድን በሰው ህይወት እና ንብረት ላይ የሚያደርሰው ጥፋት በማስተባበሩ በኩል እጁ የለበትም ማለት አይቻልም፡፡ ሆኖም የክልሉ መንግስትም ሆነ የፌደራሉ መንግስት ይህ ሴክሬታሪያት ወይ ህጋዊ የሚሆንበትን እና ካጠፋ የሚጠየቅበትን መንገድ ሲያመቻች አለያም ህገወጡ ሴክሬታሪያት ከህገወጥ ተግባሩ እንዲታቀብ ሲያደርግ አልታየም፡፡

በአንፃሩ በህጋዊ መንገድ የሲቪክ ማህበርነት ፈቃድ ለማውጣት እየተንቀሳቀሰ ያውን እና በተቻለ መጠን የአዲስ አበባን ህዘብ ውክልና ለማግኘት ህዝብን ሰብስቦ የመከረውን የባለ አደራውምክርቤት መውጣት መግባቱ በከፍተኛ የመንስት ተፅዕኖ ስር ከመውደቅ አልፎ መግለጫ መስጠት እና የመሰብሰብ መብቱ  ሲረገጥ ይስተዋላል፡፡መንግስት በአዲስ አበባ ባላደራ ምክር ቤት ላይ ያለው ከልክ ያለፈ ክትትል እና ቁጥጥር በሲዳማ ፖለቲከኞች ላይም ቢያደርግ ኖሮ ዛሬ በደቡብ ክልል የታየው አሳዛኝ የህይወት እና የንብረት ውድመት ባልታየ ነበር፡፡

ይህ የሲዳማ እና የኦሮሞ አክራሪ ብሄርተኞች የተጣመሩበትን አደገኛ አካሄድ ዝም ብሎ የማየቱ ነገር ኢትዮጵያዊ ማንነታቸውን አጥብቆ በመያዙ እንከን የሌላቸውን ሌሎች የደቡብ ክልል ብሄረሰቦችን ክፉኛ ያስቆጣ ነው፡፡የቁጣቸው ዋነኛ ማጠንጠኛ መንግስት ለፍተው ያስዋቧትን አዋሳን ለሲዳማ ፖለቲከኞች በገፀ-በረከትነት ሊያበረክት እስከ መቻል ይሄዳ የሚለው ጥርጣሬ ነው፡፡ ይህ ቁታ በፍጥነት በብሄራችን የሚቀነበብ ክልል ይፈቀድልን የሚል ጥያቄ እንዲያዥጎደጉጉ አድርጓቸዋል፡፡

ይህ ንዴት ወለድ ጥያቄ መንግስት የሲዳማ ፖለቲከኖችን እሹሩሩ ከማለቱ የተነሳ የመጣ እንጅ የደቡብ ክልል ብሄረሰቦች ከአንድ ክልል አልፎ በኢትዮጵያዊነት ጥላ ስር ለማደርም ጥበት እጅግም የማይፈትናቸው፣ለኢትዮጵያ ብሄርተኝነትም ፅኑ ምሰሶ የሆኑ ክፍሎች ናቸው፡፡የሲዳማ ልሂቃንን እራስ ወዳድነቱ ያመዘነ ጥያቄ መግራት ካልተቻለ ግን ይህ የኢትዮጵያዊነት ጠንካራ አዕማድ ሊወድቅ የማይችልበት ነገር የለም፡፡ የሲዳማ ብሄርተኞችን ጥያቄ ልጓም አስገብቶ በውል አለመያዝ ኢትዮጵያን ውድ ዋጋ የሚያስከፍል መዘዝ አለው፡፡ ይህ መዘዝ በምን ይገለፃል? የሲዳማ ፖለቲከስ እንዴት መያዝ አለበት?የሚለውን ለመዳሰስ ሳምንት ልመለስ፡፡