የሀዋሳ ከተማ ሙሉ ለሙሉ ወደቀደመው ሰላምና መረጋጋቷ መመለሷንና በአሁኑ ወቅት ያለምንም ስጋት የሚሰሩባትና የሚንቀሳቀሱባት ከተማ መሆኗን አዲሱ የከተማዋ ምክትል ከንቲባ አቶ ጥራቱ በየነ ገለፁ። ምክትል እንዳስታወቁት ከተማዋ ባለፈው ሀምሌ ከሲዳማ ዞን ክልል የመሆን ጥያቄ ጋር በተያያዘ ተፈጥሮ ከነበረው የሰላምና መረጋጋት እጦት ተላቃለች ብለዋል።

በተለይም በከተማዋ የሚገኘው የኮማንድ ፓስት፣የክልሉ የጸጥታ ሃይልና ህዝብ በጋራ ባከናወኑት ተግባር በአሁኑ ወቅት የነዋሪው ፣የንግዱ ማህበረሰብ እና የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ወደ ቀድሞው ሁኔታ ተመልሷል። ‹‹ሀዋሳ አሁን ያለምንም ስጋት የሚሰሩባትና የሚንቀሳቀሱባት ከተማ ሆናለች›› ያሉት ምክትል ከንቲባው፣ ባለሀብቶችና የንግዱ ማህበረሰብ ወደ ከተማዋ መጥተው እንዲሰሩም ጥሪ አቅርበዋል።

ቱሪስቶችም ሆኑ ለተለያዩ ስራዎች ወደ ከተማዋ መምጣት የሚፈልጉ ሁሉ ያለምንም ስጋት ወደ ከተማዋ መምጣት እንደሚችሉም ጠቁመዋል። በተለይ ኢንቨስት ለማድረግ የሚመጡ አካላትን ከተማ አስተዳደሩ ከመቼውም ጊዜ በተሻለ ለማገልገል ዝግጁ መሆኑንም አረጋግጠዋል። ከተማዋ ሰላሟና መረጋጋቷ ለመመለሱ ነዋሪው ምስክር መሆን እንደሚችል የተናገሩት ምክትል ከንቲባ ጥራቱ፣የሆቴሎች እንቅስቃሴ ከመቀዛቀዝ እየወጣ ያለበት ሁኔታም ሌላው ማሳያ መሆኑን አመልክተዋል።

ከነሀሴ 2011 መጨረሻ አንስቶም ሆቴሎች በአብዛኛው ሙሉ መሆናቸውን ጠቁመው ከተማዋ ከአንድ ሳምንት በፊት ከሁለት ሺ በላይ የክልላችን እና ከክልል ወጪ ያሉ አመራሮች ስብሰባን ከአንድ ሳምንት ላላነሰ ጊዜ አስተናግዳለች ሲሉ የከተማዋ ምክትል ከንቲባ አቶ ጥራቱ ተናግረዋል ።

አዲሱን ዓመት ፣የመስቀል ደመራንና የመስቀል በዓል ያለምንም የጸጥታ ችግር ከመቼውም ጊዜ በደመቀ መልኩ መከበራቸውም ሌላው የሰላምና መረጋጋቱ ወደ ቀድሞው ስፍራው መመለስ ማሳያ መሆኑን ምክትል ከንቲባው ጠቅሰዋል።

ሀዋሳ ከተማ ከሀምሌ 11/2011 ዓ.ም ወዲህ በሰላም እጦት ምክናየት እንቅስቃሴዋ ተዳክሞ የነበረ ሲሆን፤ እንደዚህ አይነት ችግር እንዳይመለስ እየተሠራ ነው ሲሉ ምክትል ከንቲባው አቶ ጥራቱ በየነ አስገንዝበዋል።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here