የበርካታ ነዋሪዎች ሕይወት ከጣና ሐይቅ ጋር በእጅጉ የተሳሰረ በመሆኑና ጣና ሐይቅ ለበርካቶች የኢኮኖሚ ምንጭ እንደሆነ ቢታወቅም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን የግለሰቦች ጥንቃቄ የጎደለው ዕለታዊ እንቅስቃሴ ለሐይቁ ኅልውና ስጋት መሆኑ ተነግሯል፡፡

አሁን አሁን በብዛት የፕላስቲክ ውጤቶች በሐይቁ ውስጥና ዳርቻ ተጥለው ማየት እየተለመደ  መምጣቱ እንዳሳሰባቸው የተናገሩት የአካባቢው ነዋሪዎች፤ የፕላስቲክ ውጤቶች በአብዛኛው በሐይቁ ዳርቻ ለመዝናናት ጊዜያቸውን የሚያሳልፉ ሰዎችና ኃላፊነት በማይሰማቸው ጎብኝዎች የሚጣሉ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

አንዳንድ ግለሰቦች በሐይቁ ውስጥ ልብሳቸውን ሲያጥቡ፣ ሰውነታቸውንም ሲታጠቡ ማየት የተለመደ ሲሆን ይህን ተከትሎ ለጽዳት የሚጠቀሙበት እንደ ኦሞ፣ ሳሙና፣ በረኪናና መሰል ማጽጃ ኬሚካሎች በብዝኃ ሕይወቱ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደራቸው ተነግሯል፡፡

ጉዳዩ የሚመለከተው የአማራ ክልል የአካባቢ፣ የደንና የዱር እንስሳት ጥበቃና ልማት ባለስልጣን በሐይቁ ላይ እየተስተዋሉ የሚገኙ ሰው ሰራሽ ችግሮች ማኅበራዊ ኃላፊነትን በትክክል ባለመወጣት የሚከሰቱ መሆኑን አስረድቷል፡፡ አስጎብኝዎችንና በጎ ፍቃደኛ ወጣቶችን በማስተባበር በየወሩ የጽዳት ሥራ መጀመሩንም የባለስልጣኑ አካባቢ ጥበቃና አየር ንብረት ዳይሬክተር አቶ አወቀ ይታይ ተናግረዋል፡፡

ከዚህ ባለፈ ሐይቁን እየበከሉ ያሉ ፕላስቲክ ቆሻሻዎች መልሰው ጥቅም እንዲሰጡ ለማድረግም በዘርፉ ልምድ አላቸው ከተባሉ ድርጅቶች ጋር በጋራ ለመሥራት መታቀዱን እና ከአንድ የጀርመን ድርጅት ጋርም በቅንጅት ለመሥራት ምክክር እየተደረገ መሆኑንም ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል፡፡

የባሕር ዳር ከተማ ጽዳትና ውበት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዘላለም ጌታሁን ደግሞ በሐይቁ ውስጥ የገላ መታጠብን ለመቀነስ አገልግሎት እየሰጡ ያሉ ሦስት ቋሚ የሕዝብ መጸዳጃ ቤቶች በሐይቁ አካባቢ እንደሚገኙ አብራርተዋል፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here