አባይ ሚዲያ (መስከረም 21 ፣ 2012) ክልሉን ወደ ግጭትና ሁከት እንዲገባ እየሰሩ ያሉ አካላትና ጽንፈኛ መገናኛ ብዙሃን ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ የአማራ ክልል የሰላምና ደህንነት ቢሮ አስጠነቀቀ። የቢሮ ሀላፊው አቶ አገኘሁ ተሻገር፤ እንደገለጹት የቅማንት የማንነትና የራስ አስተዳደር ጥያቄ ባለፉት ዓመታት ተነስቶ የክልሉ መንግስትና ምክር ቤቱ ተገቢ ምላሽ የሰጡ ቢሆንም በምላሹ ያልተካተቱ ቀበሌዎች አሉ በሚል ከኮሚቴዎቹ አባላት ቅሬታ ይነሳል።

ባልተስማሙበት ጉዳይ ጥያቄ ማንሳት ተገቢነት ያለው ቢሆንም ፅንፈኛ ሃይሎች ከኋላ ሆነው ሁከት እንዲፈጠር በመገናኛ ብዙሃን አማካኝነት ጉዳዩ በተሳሳተ መንገድ እንዲሄድ እያደረጉ ነው ያሉት የቢሮው ሃላፊ፤ ልዩነቱን የሚጠቀሙበት ሀይሎች የአማራ ክልል ተረጋግቶ እንዳይቀጥል ከጽንፈኛ ሃይሎች ጋር ትስስር ፈጥረዋል ብለዋል። እነዚህ ሃይሎች ከኋላ በመሆን ስልጠና በመስጠት፣ ትጥቅ በማስታጠቅና ገንዘብ በማቅረብ የተለያዩ የሽብር ስራዎችን እንዲሰሩ እያደረጓቸው እንደሆነና ዓላማውም ክልሉን ማተራመስ እንደሆነም ገልፀዋል።

 እንደ አቶ አገኘሁ ገለፃ ከኋላ ሆነው በሚደግፏቸው ሀይሎች የክልሉ ፖሊስና ተራ የመከላከያ ወታደር የማይታጠቃቸውን እንደ ስናይፐር፣ መትረየስና ሌሎች መሳሪያዎችን ታጥቀዋል። እነዚህ ሃይሎች አማራን ለማዳከም የተፈጠሩ ናቸው ያሉት አቶ አገኘሁ በጽንፈኛ ኮሚቴዎች በመታገዝ መንገድና ተቋማትን በመዝጋት፣ ሰው በመግደል፣ የመንግስትን ስራ በማስተጓጎል ክልሉን ወደ ችግር ለመክተት እየሰሩ ይገኛሉ። ሃላፊው እነዚህ አካላት ከዚህ መጥፎ ተግባራቸው ቢታገሱ የተሻለ ነው፤ ይህን ተገቢ ያልሆነ ስራቸውንም ለሚመለከተው የተናገርን ሲሆን፤ የማስተካከያ እርምጃም መወሰድ እንዳለበትም አሳስበናል” ነው ያሉት።

ከመተማ ወደ ጎንደር የሚወስደው መንገድም እስከ ትናንት መዘጋቱን ያነሱት አቶ አገኘሁ፤ በዚህም ከውጭ ወደ አገር የሚገባው ነዳጅና ሌሎች ሸቀጦች እንዳይገቡ አድርጓል ብለዋል። የሰሊጥ መሰብሰቢያ ወቅት በመሆኑ የቀን ሰራተኞች ወደዚያ እንዳይሄዱ በማድረግ ድርጊቱ የአማራ ክልልን ህዝብ ኢኮኖሚው እንዲጎዳ የማድረግ ሴራ መሆኑንም ገልጸዋል።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here