አባይ ሚዲያ (መስከረም 21 ፣ 2012) የሃይማኖት መሪዎች በአሁኑ ጊዜ ከመቼውም ጊዜ በተሻለ ሁኔታ በጋራ አገራዊ ጉዳዮች ላይ በከፍተኛ የመተባበር መንፈስ ውስጥ ቢሆኑም፣ ሃይማኖትን ሽፋን በማድረግ ከሃይማኖቶች መሠረታዊ መርህና አስተምህሮ ጋር ተቃራኒ የሆኑ ድርጊቶችን የሚፈጽሙ ጽንፈኛ አካላት በተለያዩ አካባቢዎች በመታየት ላይ መሆናቸው ተጠቆመ፡፡

ትላንት መስከረም 20 ቀን 2012 ዓ.ም የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ 11ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔው ላይ የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ሰብሳቢ ብፁዕ አቡነ ጎርጎሪዎስ እንደገለጹት፣ የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት መሪዎች ሃይማኖትንና እውነተኛነትን ወደ ምዕመናን ለማስረፅና የሁሉም ሃይማኖቶች ተከታዮች በፍፁም መከባበርና መዋደድ እንዲኖሩ፣ መሪዎቹ አርዓያ መሆን አለባቸው፡፡ ሰብሳቢው አክለውም የአገር ሰላምና አንድነት ሳይደናቀፍ እንዲቀጥል ማድረግ ከፈጣሪም ሆነ ከሚያገለግሉዋቸው ምዕመናን፣ የተጣለባቸውን ከፍተኛ ኃላፊነትና አደራ ማስታወስ ተገቢ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ አልማዝ መኮንን በበኩላቸው ‹‹ኢትዮጵያውያን በሃይማኖቶች መካከል ለዘመናት በጥልቅ መሠረት ላይ የተገነባ የመከባበርና በሰላም አብሮ የመኖር አኩሪ እሴት በተተኪ ትውልዶች ጠብቆ ለማስቀጠል የሃይማኖት መሪዎች በመተባበር እየሠሩ ይገኛሉ፤›› ብለዋል፡፡

አቡነ ጎርጎሪዎስ አክለው እንደተናገሩት‹‹ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለያዩ አካላት በማኅበራዊ ሚዲያና በልዩ ልዩ መንገዶች ሃይማኖትን ሽፋን በማድረግ እየተካሄደ ያለው ግጭት፣ አለመከባበርና ቅስቀሳ በሁሉም ሃይማኖቶች ተቀባይነት የለውም የተወገዘ ተግባር መሆኑን በመረዳትም ሁሉም ኢትዮጵያውያን መከባበርን በማስቀደም፣ ሰላማቸውንና አንድነታቸውን ነቅተው እንዲጠብቁ›› በማሳሰብ የሰላም ሚኒስትር ዴኤታዋን መልዕክት አጠናክረዋል፡፡ የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ በ11ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔው፣ የ2011 በጀት ዓመት የሥራ ክንውን ሪፖርትን አዳምጦ ለ2012 በጀት ዓመት የሥራ ዘመን በሚያከናውናቸው ዕቅዶች ላይ ውይይት አድርጓል፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here