አባይ ሚዲያ ( መስከረም 27 ፣ 2012 ) የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ ኢዜማ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ የተለያዩ ነጥቦችን በማንሳት የፓርቲውን አቋም የሚያሳውቅ መግለጫ አውጥቷል፡፡ ፓርቲው 6 የሚሆኑ ጉዳዮችን ባብራራበት መግለጫው አሁን ስልጣን ላይ ያለው ሀይል የመጣውን የለውጥ ጭላንጭል ድርግም አድርጎ በማጥፋት ወደራሱ አምባገነናዊ አገዛዝ ሊጠልፈው እንደሆነ ከበቂ በላይ ምልክቶችን አይተናል ብሏል። ኢዜማ በመግለጫው ላይ የኦዴፓ አደረጃጀት የኤሬቻ በዓልን በመጥለፍ የመቶና የመቶ አምሳ አመት የሰባሪና የተሰባሪ ትርክት ማቀንቀኑ ሀገሪቷን ወደ አንድነት ለማምጣት የሚደረገውን ጥረት ወደ ኋላ የሚጎትት እና የሚበርዝ ነው ያለ ሲሆን ይህ አይነቱነ ትርክት በአስቸኳይ እንዲታረም እንጠይቃለን ብሏል፡፡

በቅማንት እና አማራ መሀል እየተፈጠረ ላለው ችግር የፌደራል ስርዓቱን እና ‘ጠብ አጫሪ’ ያላቸውን ሚዲያዎች ያወገዘው ኢዜማ የብሮድካስት ባለስልጣን ስራዬ ብሎ ወሬ ፈብርከው ግጭቶችን የሚያዋልዱ ሚዲያዎች ላይ እርምጃ እንዲወስድባቸው በመግለጫው ጠይቋል፡፡ ፓርቲው አክሎም በማንኛውም መንገድ ህዝብን ወደ እልቂት ለመክተት የሚደረጉ የትንኮሳ አካሄዶችን እንዲያቆሙ በኢህአዴግ ውስጥ የተሰባበሱ የብሄር ድርጅቶች ያላቸውን ፓርቲዎች በጥብቅ አሳስቧል፡፡ ሌላው ኢዜማ የጠቀሰው ጉዳይ የአዲስ አበባ ፖሊስ የደንብ ልብስ እና የአደረጃጀት ለውጥን ሲሆን በተለይም አዲሱ የደንብ ልብስ ጥቅም ላይ እንዳይውል አቋሙን ገልጿል፡፡ በተጨማሪም የአዲስ አበባ ህዝብ እየደረሰበት ያለውን አፈና እስካሁን በሆደ ሰፊነት ማለፉ ሊያስመሰግነው ይገባል ያለው ኤዜማ ህዝቡ የሚደርስበትን የመብት ጥሰት በሰላማዊ መንገድ ለመቃወም  የሚያደርጋቸውን ማንኛውንም እንቅስቃሴዎች እንደሚደግፍ አስታውቋል፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here