አባይ ሚዲያ ( መስከረም 27 ፣ 2012 ) ዛሬ በባህርዳር ከፍተኛ ፍርድ ቤት የቀረቡት እነ ብ/ጀኔራል ተፈራ ማሞን ጨምሮ 76 ሰዎች እንዲሁም በእነ ስንታየሁ ታከለ መዝገብ 9 ሰዎች በባህርዳር ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቀጠሮ ችሎት ለመከታተል የባህርዳር ከተማ ነዋሪ ወደ አደባባይ የወጣ ሲሆን ከጣና ሀይቅ ትምህርት ቤት ፣ ከፓሊስ ኮሚሽን እስከ ከፍተኛ ፍርድ ቤት መንገድ ተዘግቶ ነበር ። የባህርዳር ወጣቶችና ችሎቱን ለመከታተል የታደሙ የመጡ ሁሉ የተቃውሞ ድምፅ ሲያሰሙ መቆየታቸው ታውቋል ። ችሎቱን ለህዝብ ክፍት ማድረጉ ካሁን በፊት አላስፈላጊ የሆኑ ጭብጨባዎችና ረብሻዎች በመኖራቸው ዛሬ ችሎቱ ለሁሉም ያልተፈቀደው አላስፈላጊ የሆኑ ረብሻዎችን ለማቆም እንደሆነ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የአካባቢው የፖሊስ አባል ነግረውናል ፡፡ ወደ ችሎት የሚወስደው መንገድ በመዘጋቱ ወጣቶች ከፖሊስ ጋር በፈጠሩት አለመግባባት ፖሊስ የአስለቃሽ ጭስ በመጠቀም እንዲሁም ድብደባ መፈጸሙን የአይን እማኞች ለአባይ ሚዲያ ገልጸዋል ፡፡

በተጨማሪም የእነ ብ/ጀኔራል ተፈራ ማሞ ጉዳይ ዛሬ የመጨረሻውን ውሳኔ ያገኛል ሲባል ለሌላ ጊዜ መቀጠሩ ነዋሪዎቹን የበለጠ እንዳስቆጣቸው ምንጮች ጠቁመዋል ፡፡ የእነ ብ/ጄኔራል ተፈራ ማሞ የምርመራ ጉዳይ ላይ የክልሉ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግና የፖሊስ ምርመራ ቡድን የጠየቁት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ቀጠሮ ይግባኝ ውድቅ ተደርጓል ፡፡ ጉዳዩን ሲመለከት የቆየው የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ዛሬ ረፋድ ባስቻለው ችሎት የመርማሪ ቡድኑ የጠየቀውን የተጨማሪ ቀጠሮ ይግባኝ ውድቅ አደርጓል ፡፡

መርማሪ ቡድኑ ይግባኝ ከጠየቀበት ጊዜ ጀምሮ ተጠርጣሪዎቹ ለ64 ቀናት በማረፊያ ቤት የቆዩ በመሆናቸውና መርማሪ ቡድኑ በእነዚህ ጊዜያት ውስጥ መረጃ እያጣራ ያለ መሆኑን ቀሪ ምስክሮችም ጥቂት መሆናቸውን ግምት ውስጥ በማስገባት ጥቅምት 12 ቀን 2012ዓ.ም ክስ እንዲመሠረት ትዕዛዝ በመስጠት መዝገቡን ዘግቷል፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here