አባይ ሚዲያ ( መስከረም 27 ፣ 2012 ) ግብፅ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የውሃ አሞላል ዙሪያ ያነሳችው አቋም የኢትዮጵያን ቀይ መስመር የሚያልፍ በመሆኑ ከመግባባት ላይ መድረስ እየተቻለ አይደለም ሲል የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታወቀ ። የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ምክር ቤት ፅ/ቤት በግድቡ ሁለንተናዊ ጉዳይ ላይ ከተለያዩ አካላት ጋር በዛሬው እለት የምክክር መድረክ አካሂዷል ። በመድረኩ የግድቡ ግንባታ ያለበትን ደረጃ እና የታችኛው ተፋሰስ አገራት የሶስትዮሽ ውይይት ወቅታዊ ሁኔታን በተመለከተ ሀሳቦች ተነስተው ውይይት ተደርጎበታል ። የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር የድንበርና ድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ጉዳይ አማካሪ አቶ ተፈራ በየነ በኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብፅ መካከል እየተደረገ ባለው የሶስትዮሽ ውይይት ዙሪያ ማብራሪያ ሰጥተዋል ። በማብራሪያቸውም ግብጽ በየዓመቱ 40 ቢሊየን ሜትር ኪዮብ ውሃ ይለቀቅልኝ ማለቷ እና የአስዋን ግድብ ከፍታ ከባህር ጠለል በላይ 165 ሜትር ሲደርስ ኢትዮጵያ ውሃ መልቀቅ አለባት፤ እንዲሁም ሶስተኛ ወገን በአደራዳሪነት ይግባ የሚል አቋም ማቅረቧን አንስተዋል።

ግብፅ በውይይቶቹ ላይ እያነሳች ያለው አቋም በኢትዮጵያ በኩል የህልውና እና የሉዓላዊነት ጉዳይ በመሆኑ ውድቅ መደረጉን ነው አቶ ተፈራ የገለጹት። ግብጽ በታላቁ ህዳሴ ግድብ ላይ የምታነሳቸው ሀሳቦች የኢትዮጵያን ቀይ መስመር የሚያልፍ መሆኑንም አማካሪው አንስተዋል ። ግብፅ በካርቱም በተደረገው ስብሰባ ላይም ብዙ የማያግባቡ አጀንዳዎችን ስታቀርብ እንደነበረ እና በውይይቶቹ ላይ እያሳየች በሚገኘው አቋም ደግሞ ከመግባባት ላይ መድረስ እየተቻለ አይደለም ብለዋል ። ግብፅ በታላቁ የህዳሴ ግድብ የውሃ አሞላል ላይ የምታቀርባቸው ሃሳቦችን መቀበል ማለት ያሁኑን ብቻ ሳይሆን በቀጣዩ የኢትዮጵያ ትውልድ ላይ ጉዳት የሚያደርስ በመሆኑ ተቀባይነት እንደሌለውም አስታውቀዋል ።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here