አባይ ሚዲያ (መስከረም 28፣2012) ‹ኦነግ› በሚል ሥያሜ ሁለት የፖለቲካ አደረጃጀቶች ለመመዝብ በመቅረባቸው ለምዝገባ መቸገሩን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወይዘሪት ብርቱካን ሚዴቅሳ ተናገሩ። በቀጣዩ ምርጫ የሚሳተፉ የፖለቲካ ፖርቲዎችን የመመዝገቡ ሥራ በጥሩ ሁኔታ እየተከናወነ መሆኑን የገለጹት ወይዘሪት ብርቱካን አንዳንድ ፖርቲዎች አስፈላጊውን ቅድመ ሁኔታ አሟልተዉ ስለማይቀርቡ የምዝገባ ሥራዉን እያጓተተዉ ነው።
በተለይም በኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ሥም ሁለት አካላት ለምዝገባ በመቅረባቸዉ ምክንያት አንዱን ለይቶ ለመመዝገብ መቸገሩን ምርጫ ቦርዱ አስታውቋል፡፡ ከሁለቱ አካላት በተሻለ ቅድመ ሁኔታዎችን የሚያሟላው እንደሚመዘገብና ዕዉቅና እንደሚሰጠውም ተመላክቷል፡፡
በተመሳሳይ ‹ኢዜማ› የተሰኘ የፖለቲካ አደረጃጀትም ሀገር አቀፍ ፓርቲ ሁኖ ለመመዝብ በሂደት ላይ መሆኑንም ነው ወይዘሪት ብርቱካን የተናገሩት፡፡ በሶማሌ ክልል የሚንቀሳቀሰዉ ‹ኦብነግ› የተሰኘ ፓርቲም ለምዝገባ አስፈላጊውን ቅድመ ሁኔታዎች እያሟላ እንደሆነ ታውቋል። ለቀጣዩ ምርጫ የመራጮችን ምዝገባ በጂ ፒ ኤስ ታግዞ ለማከናወን ከተለያዩ ድርጅቶች ጋር በቅንጅት እየተሠራ መሆኑ ተመላክቷል።
ባለፈዉ ዓመት ሳይካሄድ የቀረዉ የሕዝብና ቤቶች ቆጠራ ተካሂዶ ቢሆን ኑሮ በተወሰነ ደረጃ የመራጮችን ምዝገባ ሥራ ሊያቃልለዉ ይችል እንደነበርም ወይዘሪት ብርቱካን ገልጸዋል። ባለፉት ምርጫዎች የመንግሥት ሠራተኞች በየአካባቢያቸው የምርጫ ጣቢያ አስፈፃሚዎች ሁነው ይሠሩ እንደነበር የተገለፀ ሲሆን በዚህ ዓመት በሚካሄደው ምርጫ ግን ከ250 ሺህ በላይ የምርጫ ጣቢያ አስፈፃሚዎችን መልምሎ በመቅጠር ወደ ሥራ ለማስገባት መታቀዱን ቦርዱ አስታውቋል፡፡
አዲስና የተሻሻለዉ የምርጫ ሕግ በቅርቡ በፖለቲካ ፖርቲዎች ዉይይት ከተደረገበት በኋላ ሥራ ላይ እንደሚውልም ተመላክቷል። በኢትዮጵያ እስከ 130 የፖለቲካ ፖርቲዎች እንዳሉ የተገመተ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ የተወሰኑት ናቸው ከምርጫ ቦርድ ጋር በቅንጅት እየሠሩ የሚገኙት ተብሏል።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here