አባይ ሚዲያ (መስከረም 28፣2012) ላለፉት ሁለት ቀናት በድሬደዋ ከተማ ደቻቱ፣ አምስተኛ እና ገንደ ጋራ በተባሉ አካባቢዎች ለተከሰተው ግጭት መንግስት መፍትሄ ይስጠን ሲሉ የአካባቢው ነዋሪዎች ባካሄዱት ሰላማዊ ሰልፍ ጠይቀዋል። ከትላንት ወዲያ መስከረም 26 2012 እንዲሁም ትላንት መስከረም 27 2012 በአስተዳደሩ ህንፃ ፊት ለፊት የኅብረተሰቡ አካላት «ችግር ፈጣሪዎች ተጠያቂ ይሁኑ፣ አስተዳደሩ በየጊዜው ለሚፈጠረው ግጭት ዘላቂ መፍትሄ ይስጥ» የሚሉ እና ሌሎች ጥያቄዎችን ሰልፍ በማካሄድ ማቅረባቸውን የአባይ ሚዲያ ምንጮች በስልክ ነግረውናል፡፡
ከትላንት ወዲያ በደቻቱ አከባቢ የሚኖሩ ሴቶች ብቻ ሰላማዊ ሰልፍ ማካሄዳቸውን ያስታወሱት ምንጫችን ትላንት ደግሞ ሰልፉ ወንዶችም ሴቶችም በተገኙበት በአምስተኛ እና ገንደ ጋራ ተካሂዷል ብለዋል። ሰልፉ በሰላም መጠናቀቁን የነገሩን ምንጫችን ድሬዳዋ ውስጥ ግችቶች የሚነሱት ህዝብ የሚበዛባቸውና የንግድ ቦታዎች ላይ በመሆኑ ጥቃት አድራሾች ብዙ ጊዜ ንብረት ዝርፊያ ላይ ትኩረት እንደሚያደርጉ ጠቁመዋል፡፡
አባይ ሚዲያ ትላናት በግጭቱና በሰላማዊ ሰልፉ ዙሪያ መረጃ ለማግኘት ወደ ድሬዳዋ ከተማ ፖሊስ ጽ/ቤት ባደረገው ሙከራ በወቅታዊ የድሬዳዋ ጉዳይ ላይ መግለጫም ሆነ መረጃ ለመስጠት መቆጠቡን ማሳወቁን ተከትሎ ከከተማው የጸጥታ አካላት ይሄ ነው የሚባል መረጃ ማግኘት አልተቻለም፡፡ የመረጃ ምንጫችን ችግር ሲከሰት ከተማዋ በሙሉ ግጭትና ውጥረት ውስጥ ናት ማለት አይቻልም ያሉ ሲሆን ግጭት በአንዳንድ አካባቢዎች በድንገት እንደሚነሳ ጠቅሰው ከተማዋ ዘላቂ መፍትሄ ካልተበጀላት ወደፊትም ጥቃት ፈጻሚዎች መጥተው ግችት ላለመፍጠራቸው ዋስትና እንደሌለ ነግረውናል፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here