አባይ ሚዲያ (መስከረም 28፣2012) የኦሮሞ ዴሞክራቲክ ፓርቲ ኦዲፒ ዛሬ በሰጠው መግለጫ ከየትኛውም ወገን የመጡ ጨቋኝ ገዥዎች ጥቅማቸውን እንጂ የመጡበትን ወገን እንደማይወክሉ ፓርቲው በጽኑ እንደሚያምን አስታውቋል፡፡ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ሽመልስ አብዲሳ ከቀናት በፊት አዲስ አበባ በተከበረው የኢሬቻ በዓል ዋዜማ ላይ ያደረጉት ንግግር ዛሬም ድረስ የብዙዎች መከራከሪያ መሆኑ ይታወቃል፡፡
የአቶ ሽመልስ ንግግር በርካቶችን ከማስቆጣቱና ከማከራከሩ በላይ የኦዲፒ አቋም እንደሆነ በመወሰዱ በርካታ ለፖለቲካው ቅርበት ያላቸው ግልሰቦች ኦዲፒን በተረኝነት መንፈስ ከትህነግ/ህወሃት ጋር ሊያነጻጽሩት ተገደዋል፡፡ ይህንን ተከትሎ ፓርቲው ዛሬ ባወጣው መግለጫ ህዝብን ከቡድኖች ለይቶ መረዳት ይገባል ሲል ከተለመደው የሕወሃት ማብራሪያ ጋር ተመሳሳይ የሆነ የማስተካካያ መልዕክት አስተላልፏል፡፡
ኦዴፓ የአገሪቱን ህዝቦች የእኩልነት፣ የፍትሕና እና የነጻነት ጥያቄዎችን ለመመለስ፣ ከእህት ድርጅቶች እና ከአጋሮቹ ጋር ኅብረት ፈጥሮ በመታገል ላይ እንደሚገኝ ገልጿል፡፡ ፓርቲው የትግል ሂደቶቹን በተመለከተ በሦስት መርሖች እንደሚመራ የተገለጸ ሲሆን፣ በህዝቦች ታሪክ ውስጥ የነበሩ በጎ ዕሴቶችና ድሎች አክብሮና አጠናክሮ መቀጠል፤ ባለፉት ዘመናት የተሠሩ ስሕተቶችን በጋራ ነቅሶ ማረም፣ እንዲሁም ካለፈው ትምህርት ወስዶ ተጨማሪ ስሕተቶችን ባለመድገም እንደሆነ አስረድቷል፡፡
እነዚህን የትግል መርሖች ለማሳካት የሚደረጉ ንግግሮችና ተግባሮች ሁሉ በሕዝቦች መካከል ፍቅር፣ አንድነትና ሰላም የሚያመጡ መሆን እንዳለባቸው የኦዲፒ ጽኑ እምነት እንደሆነና ከዚህ በተቃራኒ የሚፈጸሙትንም በድርጅቱ ባህል መሠረት እንደሚታረሙ ፓርቲው ገልጿል፡፡ ከየትኛውም ወገን የመጡ ጨቋኝ ገዥዎች ጥቅማቸውን እንጂ የመጡበትን ወገን እንደማይወክሉ ፓርቲው በጽኑ እንደሚያምን የገለጸው ፓርቲው፣ ባለፉት ዘመናት ሲደረጉ የነበሩት መራራ ትግል ከጨቋኝ ገዥዎች ጋር እንጂ ከሕዝቡ ጋር እንዳልነበረና ሕዝቦች ሲጨቆኑ እንጂ ሲጨቁኑ እንዳልኖሩ ፓርቲው አመልክቷል፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here