አባይ ሚዲያ (መስከረም 28፣2012) የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) ያሉበትን ድክመቶቹን ለማረም እየሰራ መሆኑን የፓርቲው ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል አቶ ንጉሱ ጥላሁን ገለጹ። ፓርቲው በአሁን ወቅት የሚመራው በራሱ እንጂ ማንም አካል በሚሰጠው መመሪያ አለመሆኑንም ነው የገለጹት።ባለፈው አመት ጀምሮ በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ዛሬም ድረስ ግጭቶች አልፎ አልፎ መኖራቸው ክልሉን ከግጭት ነጻ እንዳይሆን አድርጎታል፡፡
በተለይም በተደጋጋሚ ግጭቱን ሙሉ በሙሉ መከላከልም ሆነ መቆጣጠር ላለመቻሉ ዋናው ተጠያቂ የክልሉ ገዢ ፓርቲ አዴፓ እንደሆነ በክልሉ የሚገኙ የፖለቲካ አደረጃጃቶችን ጨምሮ የማህበረሰብ አንቂዎች በተደጋጋሚ ገልጸዋል፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞም አዴፓ የክልሉም ሆነ የኢትዮጵያ ህዝቦች የሚያነሷቸውን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመመለስ እየታገለ መሆኑን አቶ ንጉሱ የገለጹ ሲሆን ፓርቲው በሚያከናውናቸው ስራዎች ላይ እያጋጠሙ ያሉ ድክመቶችን ለማስተካከል ጥረት በማድረግ ላይ መሆኑን አንስተዋል።
በተያያዘ መረጃ አንዳንድ መገናኛ ብዙሃን የአማራ ክልልን ሰላምና ጸጥታ ለማወክ የጀመሩትን ዘመቻ በአፋጣኝ እንዲያቆሙ የፓርቲ አመራሮች ጠይቀዋል። የአገሪቷ የለውጥ ሂደት ከታገለባቸው ጉዳዮች መካከል የመገናኛ ብዙሃን ነጻነት አንዱ ሲሆን በዚህም በአሸባሪነት ጭምር ተፈርጀው የነበሩና በአገር ውስጥ እንዳይሰሩ የተከለከሉ አንዳንድ የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት ጭምር በነፃነት እንዲሰሩ ፍቃድ የተሰጣቸው መሆኑንም አስተያየት ሰጪዎቹ ገልጸዋል።
ይሁንና ነጻነታቸውንና ሃላፊነታቸውን ባላጣጣመ መልኩ የአማራ ክልልን ሰላምና ጸጥታ የሚያደፈርሱና ከእውነት የራቁ መረጃዎችን የሚያሰራጩ አንዳንድ የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት ከድርጊታቸው ሊቆጠቡ ይገባል ነው ያሉት። የብሮድካስት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ጌታቸው ድንቁ በበኩላቸው የብሮድካስት አዋጁን በሚጻረር መልኩ መረጃ የሚያሰራጩ የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት መኖራቸውን አምነው መገናኛ ብዙሃን የተሰጣቸውን ነጻነት በሃላፊነት መንፈስ ሊጠቀሙ እንደሚገባ አሳስበዋል።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here