አባይ ሚዲያ ( መስከረም 29 ፣ 2012 ) የኢትዮጵያ ፓርላማ በውስጡ ካካተታቸው ዕድሜ ጠገብና ሙሉ ለሙሉ ከድንጋይ የተሠሩ የሕንፃ ክፍሎችን ለማፍረስ የፓርላማው ጽሕፈት ቤት መወሰኑ ቅሬታ እንዳስነሳ ታወቀ፡፡

ቅሬታ የተሰማቸው የአስተዳደር ሠራተኞች እንደገለጹት፣ የበላይ አመራር አካላት በቂ ጥናትና ዳሰሳ ሳያደርጉ፣ ለጊዜው የተፈጠረውን የቢሮ እጥረትን ለማስተካከል በሚል ዕሳቤ ብቻ ከተገነቡ 88 ዓመት የሞላቸው የድንጋይ ቤቶችን በማፍረስ ባለአራት ወለል ሕንፃ ለመገንባት ተዘጋጅተዋል፡፡

የማፍረስ ሥራውን ለማከናወንም የማሽነሪና የመሣሪያ አቅርቦት እየተካሄደ ሲሆን፣ በሚቀጥሉት ሳምንታት የድንጋይ ቤቶቹ እንደሚፈርሱ ምንጮች  ገልጸዋል፡፡ በጽሕፈት ቤቱ ሥር የሚገኙ ሠራተኞች ፓርላማው ከተከራየው ሕንፃ ወደ ዋናው ግቢ መመላለሱ አስቸጋሪ ስለሆነባቸውና ለሥራቸውም አመቺ አለመሆኑን ባሰሙት ቅሬታ መሠረት፣ ፓርላማው አዲስ ሕንፃ ለመገንባት በዝግጅት ላይ ነው ተብሏል፡፡

ባለፈው ሳምንት የጽሕፈት ቤቱ አመራሮች አዲስ በሚገነቡትና በሚፈርሱት ነባር ሕንፃዎች ዙሪያ ባደረጉት ውይይት ክርክር መነሳቱ ታውቋል፡፡ በተለይ ሁለቱ የድንጋይ ቤቶች ‹‹መፍረስ አለባቸው›› በሚሉና ‹‹መፍረስ የለባቸውም በታሪክ ቅርስነት መቆየት ይገባቸዋል›› በሚሉ የስብሰባው ተሳታፊዎች መካከል ከረር ያለ ክርክር ተነስቶ እንደነበር ማረጋገጥ ተችሏል፡፡

ይገነባሉ ስለተባሉትና ስለሚፈርሱት ቤቶች የጽሕፈት ቤት ኃላፊዋ ዶ/ር ምሥራቅ መኮንን ስለሚገነቡት ሁለት ሕንፃዎችና የዲዛይን ሒደቱን ያረጋገጡ ሲሆን፣ ስለሚፈርሱት ሁለት ታሪካዊ ቤቶች ግን ከመናገር ተቆጥበዋል፡፡

‹‹ከፓርላማው በላይ ለቅርስ መቆርቆር ያለበት ሌላ አካል የለም፡፡ እንዲሁ ቅርስ እያወደመ ሌላ ነገር አይሠራም፤›› ያሉት የጽሕፈት ቤቱ ኃላፊዋ፣ አሁንም ቢሆን ለሚሠራው አዲስ ሕንፃ በተለይ ለዋናው የፓርላማው ሕንፃና ሌሎች ተዛማጅ ሕንፃዎች ታሪካቸውንና ዕድሜቸውን ባገናዘበ፣ እንዲሁም ደኅንነታቸውን በጠበቀ መልኩ ግንባታው እንደሚካሄድአክለው ገልጸዋል፡፡