አባይ ሚዲያ ( መስከረም 29 ፣ 2012 )  “ህውሓትን ተው ካላሉት የክልሉ ንጉስ ሆኖ መቀጠል ይፈልጋል፤ ይህ ደግሞ ለእኛ ስጋት ነው” ሲሉ የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ትብብር ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበር ኢንጂነር ግዳይ ዘራጺዮን ተናገሩ፡፡

የትዴት ም/ሊቀመንበሩ ኢንጂነር ግደይ ለአባይ ሚዲያ በስልክ እንደገለጹት ህወሃት ኢህአዴግ  በበላይነት ስልጣኑን ተቆናጦ በነበረው ጊዜ ኢህአዴግ ውስጥ የነበሩ ፓርቲዎች እኩል ስልጣን አልነበራቸውምያሉ ሲሆን አሁን ግን የኢህአዴግን ውህደት ፍትሀዊ ለሆነ የስልጣን ክፍፍል ጥሩ አጋጣሚ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

ኢንጂነር ግደይ እንዳሉት ኢህአዴግ ውህደት ፈጽሞ አንድ ፓርቲ ሆኖ፣ ይመራበት የነበረው አይዲዮሎጂ የሚቀየር ከሆነ ለተቃዋሚዎች የተሻለ ምህዳር ይፈጥራል የሚል እምነት እንዳላቸውም አመልክተዋል፡፡

ነገር ግን ህወሃት በኢህአዴግ ውህደት ካልተስማማና ተው ካላሉት የትግራይ ክልል ንጉስ ሆኖ መቀጠል ይፈልጋል፤ ይህ ደግሞ ለእኛ ትልቅ ስጋት ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ህወሃት በትግራይ ክልል ሌላ ተፎካካሪ እንዳይኖር ባለመፈለጉ በተለይዩ አጋጣሚዎች ካድሬዎቹን በማሰማራት ጥቃት በመፈጸም ሌሎች እንደሚያዳክም ም/ሊቀመንበሩ አመልክተዋል፡፡ የሕወሃት አመለካከት ሌላ ፓርቲ በክልሉ እንዲንቀሳቀስ ካለመፈለግ እንደሆነ ኢንጂነር ግደይ ዘርዓጽዮን አክለው ገልጸዋል፡፡