ነፍጠኛ ነኝ እኔ (ከድሚልኝ ብዕሬ)

አርባ ድፍን ዓመት
ተረት ሲፈበረክ፤
ሃያ ሰባት ዓመት
ቱልቱላ ሲተረክ፤
በእንግዴ ልጅ መሪ
ጥላቻ ሲሰበክ፤
እቤተኛው መጤ
የነፍጠኛው ታሪክ፤
አክራሪው ጠባቡ
ሲያጥላላ ምኒልክ፤
በስሙ በዝናው
ክፉኛ ሲታወክ፤
ለአፍሪቃዊ ክብሩ
ትንሽ ሳይል በርከክ፤
ለቆመበት መሬት
ምስጋናንም ሳይልክ፤
በዓለ እሬቻውን
በአዲሳባ ሊያመልክ፤
ጀግና ባቋቋማት
ከተማ ንትርክ፤
ፍቅር ሰላም ብሎ
በደልን ሲያስታክክ፤
የተኛው ተነሳ
ሊያስታጥቀው በልክ፡፡
ነፍጠኛ ነፍጠኛ
ነፍጠኛ ነኝ እኔም፤
አባቴም አያቴም
የምንኮራ ሁሌም፤
ወራሪ የመከትን
ትናንትናም ዛሬም፤
በነፍጥና በጦር
በሕይወትም በደም፤
በማይጨው በሽንፈት
በአድዋ ድልም፡፡
አማራው ወንድሜ
ሰሜን ላይ ያለኸው፤
ኦሮሞ እህቴ
ምዕራብ የከተምሽው፤
ጉራጌው አጎቴ
ደቡብ ላይ ያለፍከው፤
ልጆች ዘመዶቼ
እትብት በየቦታው፤
ወዳጅ ጎረቤቶች
ሁሉም በየጎራው፤
እኔ ነፍጠኛ ነኝ
እናንተም እንደዚያው፡፡
ሰባሪ አንደኛው
ተሰባሪ ሌላው፤
ቅል የመሰለው ቂል
ሽመል የመዘዘው፤
አልቃሽ አስለቃሹ
ታየ በየፊናው፤
ገሪባ አረማሞ
በቀለ ከጓሮው፤
በዳይ አስበዳዩ
ተረኛ ነኝ ያለው፤ ፤
ወረፋ የያዘው
ጊዜ የሚጠብቀው፤
ሊረዳ ያልገባው
ሁሉም በሃገር ነው፡፡
ኸረ ትርክት ትርክት
ተአምር በሉ ሰዎች፤
ማየት ጀምረናል
ጉግ ማንጉግ ፍጥረቶች፤
አሳይ መሲህ እንስሶች
እንቶ ፈንቶ ጅሎች፤
ጋዋን ያጠለቁ
የቁጩ ልሂቆች፤
ድኩም ከሃዲዎች
የሐሰት ምስክሮች፤
የኪቦርድ አንበሶች
የሚዲያ ጀግኖች፤
የከተማ አርበኞች
የመንጋ መሪዎች፡፡
ክርስቲያን ኦሮሞን
አማራ ደልዳዮች፤
ሙስሊሙን እንዲሁ
ዘረኛ ደላሎች፤
ሃይማኖትን ዘርን
ቁጭ ይበሉ ዳኞች፤
ኢትዮጵያ ቅኝ ገዢ
ታሪክ ኮማሪዎች
ሃሳብ ተረት ተረት
ቅጥፈት ቆማሪዎች፡፡
መደመር ነው ሲባል
መቀነስ ዘምታለች፤
ማባዛት ማካፈል
ሂሳብ ቆዝማለች፤
ብርሃን በጭለማ
አጉል ተጋርዳለች፤
ክፉ በጎ ሆና
ሐሰትም ነግሳለች፤
ክህደት በእምነት ላይ
የበላይ ሆናለች፤
እውነት ውሸት ሆና
ሃቅ ታጣጥራለች፤
ነፍጠኞች ፀልዩ
ፍትህም ታማለች፤
ሀገሬ አትዮጵያ
ሱባኤ ገብታለች፤
እግዜር ይማፀናት
በድል ትወጣለች፡፡
***** *** *****
፪፱ መስከረም ፪ ሺ ፲፪ | 10 ኦክቶበር 2019
© ድሚልኝ ብዕሬ—ዘአዲሱ ገበያ