አባይ ሚዲያ (ጥቅምት 1፣2012) ከጎጃም ወደ አዲስ አበባ የሚወስደው መንገድ ከትናንት ረፋድ ጀምሮ ኦሮሚያ ክልል ጎሃ ጽዮን አካባቢ በመዘጋቱ የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች ማለፍ አልቻሉም፡፡ ከጎንደርና ጎጃም ሁሉም አካባቢዎች በመነሳት ወደ አዲስ አበባ ጉዞ ላይ የነበሩ ሁሉም የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች እንዳያልፉ በመከልከላቸው ተጓዦቹ ለከፋ እንግልት ተዳርገዋል፡፡ ወደ ዩኒቨርሲቲ የሚገቡ ተማሪዎች፣ ለሕክምና ክትትል የሚሄዱ ታካሚዎች፣ በሃይማኖታዊ ጉዞ የነበሩ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች፣ ነጋዴዎችና ቤተሰብ ለመጠየቅ የሚጓዙ ሁሉ ናቸው ለእንግልት የተዳረጉት፡፡ መንገዱ ጎሀ ጺዮን ላይ መዘጋቱን ተከትሎ ቁጥራቸው ቀላል ያለሆኑ ተጓዦች ደጀን ከተማ ለመጠለልና ለማደር መገደዳቸውን የደጀን ከተማ ፖሊስ ጽሕፈት ቤት ለአባይ ሚዲያ በስልክ ተናግረዋል፡፡
የደጀን ወረዳ አስተዳደርና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ካሳ አስፋው በበኩላቸው ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ በርካታ ተሽከርካሪዎች ደጀን ከተማ እንደቆሙ አድረገዋል፤ ተማሪዎችም የምዝገባ ጊዜ እያለፈባቸው ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡ ‹‹ከባሕር ዳር መግቢያ እስከ ዓባይ አፋፍ ድረስ ደጀን ከተማ ላይ በሁለቱም አቅጣጫ መኪና ቆሟል፤ የዓባይ ባስ ክሲዮን ማኅበር ከ25 በላይ አውቶቡሶች ግን ተሳፋሪዎችን ይዘው ወደመጡበት ትናንት ተመልሰዋል›› ብለዋል ኃላፊው፡፡ የምሥራቅ ጎጃም ዞን ፖሊስ መምሪያ ተወካይ ኃላፊ ኮማንደር ግርማ ጫኔ ከኦሮሚያ ክልል መሪዎች ጋር በጉዳዩ ዙሪያ እየተነጋሩ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
‹‹መንገዱን የዘጋው በየቦታው ያለ ወጣት ነው፤ ለወጣቶቹም ተልዕኮ የሰጠ የመንግሥት አካል የለም›› መባላቸውን የገለጹት ኮማንደር ግርማ እንዲሁ በወጣቶች ከተዘጋ ወዲያውኑ ፖሊስ ሊያስከፍተው ይገባ እንደነበር አመልክተዋል፡፡ የከተማው ፖሊስ እንደነገሩን የመንገዱ መዘጋት አላማ ምናልባትም ከጥቅምት 2 የአዲስ አበባ ሰልፍ ጋር የሚገናኝ ከሆነ ቀድሞውኑ በሚዲያ ማሳወቅ እንጂ የመንገደኞች መጉላላት ተገቢ አይደለም ብለዋል፡፡
አይይዘውም መንገዱ በአስቸኳይ እንዲከፈት መንግሥት መሥራት እንዳበለትም አስገንዝበዋል፡፡