አባይ ሚዲያ (ጥቅምት 2 ፤ 2012) ችግሩን ፈጥረዋል ተብለው የተጠረጠሩ ከ90 በላይ ግለሰቦችም በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ተገልጿል። ባለፈው በጎንደር ከተማ እና በማዕከላዊ ጎንደር ዞን የጸጥታ ችግር መፈጠሩን ተከትሎ በጎንደር ከተማ ሕዝባዊ ውይይት ተደርጓል።

የጎንደር ከተማ አስተዳደር ሰላም ግንባታና የሕዝብ ደኅንነት መምሪያ ኃላፊ አቶ ተስፋ መኮንን ባቀረቡት የመወያያ ጽሑፍ ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ ሲገለጽ እንደነበረው የግጭቱ መነሻ የቅማንት የማንነት እና የራስ አስተዳደር ጥያቄ አለመሆኑን ለውይይቱ ተሳታፊዎች አስረድተዋል።

ይልቁንም የግጭቱ ዋነኛ ጠንሳሽ ህወሃት እንደሆነ፣ የማንነት እና የራስ አስተዳደር ጥያቄን እንደ ሽፋን በመጠቀም እና የጥፋት ሀይሎችን በማሰለፍ የገንዘብ እና የሎጂስቲክስ እርዳታ እያደረገ እንደነበርም ነው በጽሑፋቸው ያቀረቡት። የፖለቲካ መሪዎች፣ ወጣቶች፣ የሀይማኖት መሪዎች እና ሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎች ችግሮች እንዳይባባሱ የጎላ ሚና እንደነበራቸውም አቅርበዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎችም ችግሩን የፈጠሩት አካላት የቅማንትን ሕዝብ እንደማይወክሉ ተናግረው የሰላም መደፍረሱ በተጠና መልኩ የተሰራ መሆኑንም አንስተዋል። ችግሮች ከመነሳታቸው አስቀድሞ ስለስጋቱ መረጃ ሰጥተው እንደነበር የተናገሩት  ተሳታፊዎች የጸጥታ አካላት በሚያሳዩት ቸልተኝነት ተደጋጋሚ ችግሮች መፈጠራቸውን አስረድተዋል፡፡

በመንግስት መዋቅር ውስጥ ሆነው ሕዝብን ከሕዝብ ለማጣላት ከጽንፈኞች ጋር የሚሰሩ አካላትንም የክልሉ መንግስት መፈተሽ እና ውስጡን ማጥራት እንዳለበት ተናግረዋል።

የጎንደር ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር ሰጤ ስርግው በበኩላቸው ፋኖ እና የጎንደር ከተማ ወጣቶች ችግሩን በማርገብ ረገድ ከፀጥታ ኃይሉ ጋር በርካታ ሥራ መሥራታቸውን አስታውቀዋል። የፀጥታ ችግር ፈጥረዋል ተብለው የተጠረጠሩ ከ90 በላይ ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውንም ተናግረዋል።

በቀጣይም በተሳሳተ መንገድ ለህወሃት ተላላኪ የሆኑ አካላትን የማስተማር እና ከዚያም አልፎ ለህግ የማቅረብ ሥራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አሰታውቀዋል።