አባይ ሚድያ(ጥቅምት 2፣2012) እስረኞችን ወርኃዊ ደመወዝ እየተከፈላቸው በግብርና ኢንዱስትሪዎች እንዲሳተፉ መብት የሚሰጥና ለሰብዓዊ መብቶቻቸውም ከፍተኛ ጥበቃ እንዲደረግላቸው የሚደንግገው ረቂቅ አዋጅ ላይ ፓርላማው ተወያይቶ በዝርዝር እንዲታይ ወሰነ፡፡
አዋጁ ባሳለፍነው ሐሙስ መስከረም 29 ቀን 2012 ዓ.ም. ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበ ሲሆን ረቂቅ አዋጁ በሥራ ላይ የሚገኘውን የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር፣ የማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን በሚል ስያሜ በአዲስ መልክ ለማቋቋም የተዘጋጀ እንደሆነም ለማወቅ ተችሏል፡፡
ከዚህ ባለፈ ታራሚዎችና የቀጠሮ እስረኞች እንደማንኛውም ዜጋ ከሚዲያ አካላት ጋር ቃለ መጠይቅ የማድረግ፣ ሰብዓዊ ክብርን ከሚያዋርድ፣ ጭካኔ ከተሞላበትና ጤንነታቸውን አደጋ ላይ ከሚጥል አያያዝ የመጠበቅ መብታቸውን የሚያረጋግጠው አዋጁ፤ የሚቋቋመው ኮሚሽን የአሠራር ሥርዓቶች፣ የሚሰጣቸው ውሳኔዎች ወይም የሚፈጽማቸው ተግባሮች ዋና ዓላማ እስረኞች በማረሚያ ቤት ቆይታቸው ታርመውና በመልካም ሥነ ምግባር ታንጸው ሕግ አክባሪ፣ ሰላማዊና አምራች ዜጎች ሆነው ወደ ኅብረተሰቡ እንዲቀላቀሉ ማድረግ እንደሆነም በረቂቁ ተቀጧል፡፡
የማረሚያ ቤት ኮሚሽኑ የእስረኞችን ሰብዓዊ መብቶች በጠበቀ ሁኔታ መያዙን ለመከታተልና ለመቆጣጠር የውጭ ቁጥጥር ስልትን ጨምሮ ፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴዎችና አባላትና የእንባ ጠባቂ ተቋም፣ እንዲሁም በሕግ የማረሚያ ቤትን የመቆጣጠርና የመጎብኘት ሥልጣን የተሰጣቸው አካላት በማንኛውም ጊዜ ያለቅድሚያ ማስጠንቀቂያ ማረሚያ ቤቶችን የመጎብኘት፣ ቅሬታ ያላቸውን እስረኞች የማነጋገር፣ የእስረኞችን መዝገብ የመመርመር፣ የማረሚያ ቤት ሠራተኞችን፣ ፖሊሶችን እንዲሁም ኃላፊዎችን የማናገርና ውጤቱን ከማሻሻያ ሐሳብና ዕርምጃ ጋር ለሚመለከታቸው የመንግሥት አካላትና ለሕዝብ የማሳወቅ ሥልጣን በረቂቁ ተሰጥቷቸዋል፡፡
ፓርላማው በረቂቁ ላይ የመጀመሪያ ውይይት አድርጎ በዝርዝር እንዲታይ ለሕግ ፍትሕና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቶታል።