አባይ ሚዲያዜና – ጥቅምት 3 ፣ 2012

የአማራ ክልል የመንግስት የልማት ድርጅቶች በአዲስ አበባ የሚያስገነቧቸው የዋና መስሪያ ቤት ህንጻዎች ለክልሉ የመንግስት መስሪያ ቤቶች እንደ መቀመጫነት ከማገልገላቸው ባለፈ የክልሉ ዜጎች፣ የመንግስት መስሪያ ቤቶች፣የግል ድርጅቶች በአዲስ አበባ ያላቸውን የእኩል ተጠቃሚነት መብት የሚያረጋግጥ መሆኑን የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተመስገን ጥሩነህ ገልጸዋል፡፡ የአማራ መልሶ መቋቋም እና ልማት ድርጅት (አ/መ/ል/ድ) በአዲስ አበባ የሚያሰራው የዋና መስሪያ ቤት ግንባታ አርባ አምስት  በመቶ መጠናቀቁን እና በቀጣይ አንድ አመት ተኩል ግንባታው ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ አ/መ/ል/ድ ዋና መስሪያ ቤቱን አዲስ አበባ እንደሚያደርግ እና አዲስ አበባ የሁላችንም በመሆኗ የአማራ ክልል ተወላጆች እና የአማራ ክልል መንግስት በከተማዋ ላይ አቅማቸው በፈቀደላቸው አማራጮች ሁሉ የመጠቀም መብታቸው የተረጋገጠ ነው ሲሉ አቶ ተመስገን ጥሩነህ ገልጸዋል፡፡

በአሁኑ ሰዓት አዴፓን  ጨምሮ ሌሎች መስሪያ ቤቶች በአዲስ አበባ የራሳቸውን ህንጻ ገንብተው መቀመጫ ያላቸው ሲሆን በቀጣይ አማራ ብድር እና ቁጠባ ተቋም አ/ብ/ቁ/ተ፣የአማራ ገጠር መንገድ፣ የአማራ ባህል ማዕከል በአዲስ አበባ የሚገነቡ ይሆናል ሲሉ የጥረት ኮርፖሬት ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶክተር አምላኩ ተናግረዋል፡፡ በአዲስ አበባ ስልሳ ስምንት ከመቶ የሚሆኑት ነዋሪዎች የአማራ ተወላጆች መሆናቸውን የማዕከላዊ ስታቲክስ ኤጀንሲ ያወጣው መረጃ ያመለክታል፡፡