አባይ ሚዲያ(ጥቅምት 3፣2012) 12ኛው የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ቀን “ሰንደቅ ዓላማችን የብዝኃነታችን ድምር ውጤትና የአንድነታችን ምሰሶ ነው” በሚል መሪ ሐሳብ ዛሬ ተከብሯል፡፡ ባለፉት ረዥም ዓመታት ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ እና ለሀገሪቱ ነፃነት የተደረጉ ትግሎች የሪፐብሊኩን ሰንደቅ ዓላማ የሉዓላዊነት መገለጫና ለሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ አንድነት ምልክት መሆኑ ላይ ሰፊ የግንዛቤ ሥራ መሠራቱን የህዘብ ተወካዮች ምክር ቤት በመግለጫው ጠቅሷል።
የሰንደቅ ዓላማ ቀን በየዓመቱ ሲከበር በሪፐብሊኩ ሰንደቅ ዓላማ ዙሪያ ጥናቶች እየቀረቡ ግልጽነት ቢፈጠርም ሰንደቅ ዓላማው ሉዓላዊነት መገለጫና ለሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ አንድነት ምልክት መሆኑ ላይ የጎላ ልዩነት ባይኖርም በዓርማው ላይ ግን በሚፈለገው ደረጃ ብሔራዊ መግባባት መፍጠር አለመቻሉን ተናግሯል። እንዲህ ዓይነት ልዩነቶች ሲኖሩ በሕጋዊና ዴሞክራሲያዊ መንገድ ከሕዝብ ጋር በሚኖር ውይይት የሚነሱት ጥያቄዎች እየተመለሱና መግባባት እየተፈጠረባቸው እንደሚሄድ ጠቁሟል።
የሀገሪቱ ዜጎችም በልዩነት በሚያነሷቸው ጉዳዮች ላይ የተደራጀ ውሳኔ እስኪሰጥ ድረስ በሕግ የጸደቀውን የሪፐብሊኩን ሰንደቅ ዓላማ በማክበር ላይ አቋም እንዲይዙ ማድረግ እንደሚያስችል ምክር ቤቱ በመግለጫው ተመልክቷል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ እውቁ ፖለቲከኛ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ በአባይ ሚዲያ የአንግዳችን ፕሮግራም ላይ ከባልደረባችን መዓዛ ሙሀመድ ጋር ባደረጉት ቆይታ ስለ ሰንደቅ አለማ እንደተናገሩት ከሳምንታት በፊት አዲስ አበባ ከተማ በተከበረው የመስቀል በዓል ላይ ኮከብ የሌለው ባንዲራ ተከልክሏል በሚል በየመንገዱ ላይ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ምልክት ያለው ነገር ሲጣል ማየት ያሳዝናል ብለዋል፡፡