አባይ ሚዲያ ዜና – ጥቅምት 4፣ 2012

በሀገሪቱ ታይቶ የነበረውና ብዙ ተስፋ የተጣለበት የኢህአዴግ የለውጥ አየር በአሁኑ ወቅት ሊቀለብሱት ከጫፍ የደረሱ በርካታ ነገሮች መኖራቸውን የቀድሞው የአርበኞች ግንቦት ሰባት ጸሀፊ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ለአባይ ሚዲያ ተናግረዋል፡፡

አቶ አንዳርጋቸው እንዳሉት ኢህአዴግ በአሁኑ ወቅት ሀገሪቷን ከሚከፋፍሉ እንቅስቃሴዎች ተመልሶ ወደ አንድነት እንምጣ በሚል አካሄድ የፈጠረው ለውጥ በተለያዩ መንገዶች እየተቀለበሰ ሲሆን በተለይም ከለውጡ አላማ ጋር በቀጥታ የሚጻረሩ በዘር ላይ የተመሰረቱ ሚዲያዎች መከፋፈልን እንጂ አንድነትን ሲሰብኩ አይታይም ብለዋል፡፡

በዘር ላይ የተመሰረቱ ሚዲያዎች በዜጎች መካከል መራራቅ እንዲፈጠርና አንዱ አንዱን እንደ ጠላት በማየት ለጦርነት እንዲዘጋጅ በሚጋፋፋ መልኩ እየሰሩ ናቸው ያሉት አቶ አንዳርጋቸው ይሄ ደግሞ ለውጡ ይዞት ከተነሳው አላማ ጋር እንደሚጋጭ ጠቁመዋል፡፡

አቶ አንዳርጋቸው አክለውም በተለያዩ አካባቢዎች የተፈጠሩ ግጭቶችና መፈናቀሎችም ለውጡ ይዞት ከተነሳው ሀገርን ወደ አንድነት የማምጣት አካሄድ ጋር ይጋጫል ብለዋል፡፡

ከቀናት በፊት ወደ አዲስ አበባ የሚያስገቡ መንገዶች ተዘግተው ተሽከርካሪዎች እንዳያልፉ መደረጉ አሁንም ከለውጡ ይልቅ ከፋፋይ ሀይሎች አቅም አንዳላቸው የሚያሳይ እንደሆነ የገለጹት አቶ አንዳርጋቸው በአጠቃላይ በሀገሪቱ የምናስተውላቸው እንቅስቃሴዎች ለውጡን ለመቀልበስ የተዘጋጁ ናቸው ሲሉ ተናግረዋል፡፡