አባይ ሚዲያ ዜና – ጥቅምት 4፣ 2012

የአፋር ህዝብ የሚደርስበትን ጥቃት እና ግድያ በመቃወም በአዋሽ አርባ ሰላማዊ ሰልፍ መደረጉን ከስፍራው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

በአፋር አዋሳኝ በሆኑ ወረዳዎች ላይ ከጅቡቲ መነሻቸውን ያደረጉ ታጣቂዎች የተባሉ አካላት በተደጋጋሚ በሰላማዊ ህዝብ ላይ ጥቃት በማድረስ በርካታ ዜጎች መገደላቸውን መዘጋባችን ይታወሳል፡፡

ይህን ተግባር መንግስት እንዲያስቆም እና ተገቢውን የቅድመ መከላከል ተግባር እንዲፈፀም የሚጠይቅ ሰላማዊ ሰልፍ በአፋር አዋሽ አርባ ከተማ በዛሬው እለት ተካሂዷል፡፡

በሰልፉ ላይም የአፋር ህዝብ ለኢትዮጵያ ምኑ ነው፣በውጭ ወራሪ ሐይል ለሚሞተው ንፁሃን የአፋር ህዝብ ፍትህ ይሻል፣መንግስት ድንበር ላይ ጥብቅ ቁጥጥር ያድርግ የሚሉ እና ሌሎችም መፈክሮች ተሰምተዋል ።

ሰላማዊ ሰልፉን ምክናያት በማድረግ መንገድ መዘጋቱ የተገለጸ ሲሆን አባይ ሚዲያ በጉዳዩ ዙሪያ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ባደረገው ማጣራት የፌደራል ትራንሰፖርት አስተዳደር የአዋሽ አርባ ተወካይ አቶ አብዱልፈታህ የሰልፉን መካሄድ አረጋግጠው ከሰአታት በኋላ መንገዱ መከፈቱን ነግረውናል፡፡

አቶ አብደልፈታህ እንደሚሉት ጥቃቱ ለረጅም አመታት የኢሳ ጎሳዎች የሚባሉት የአፋር ህዝብ ላይ ለሚያደርሱት ጥቃት ከጅቡቲ ታጣቂዎች ድጋፍ እንደሚያገኙ ሰላማዊ ሰልፍ የወጣው ህዝብ ይረዳል ብለዋል፡
አቶ አብደልፈታህ እንዳብራሩት ጉዳዩ መፍትሄ ያጣ የብሄር ግጭት ሲሆን ዛሬ በተካሄደው ሰላማዊ ሰልፍ የአፋር ህዝብ ላይ የሚደርሰውን ጥቃት ለመቃወም መሆኑን ገልጸው ተቃውሞው ምናልባትም መንገዱን ለተከታታይ ሶስት ቀናት መንገድ በመዝጋት ለማካሄድ የታሰበ እንደሆነ ነግረውናል፡፡