አባይ ሚዲያ ዜና – ጥቅምት 4፣ 2012

የወልድያ-ቆቦ-አላማጣ መንገድ እንደተዘጋ ተደርጎ የሚወራው መረጃ የተሳሳተ መሆኑን የአካባቢው ነዋሪዎች እና የሥራ ኃላፊዎች ተናገሩ፡፡

ከሰሞኑ አንዳንድ የብዙኃን መገናኛ ከትግራይ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች አንስቶ በአላማጣ-ቆቦ-ወልድያ-አዲስ አበባ የሚወስደው መንገድ ከተዘጋ ዓመታት እንደተቆጠሩ እየዘገቡ መሆናቸው ይታወቃል፡፡

በትግራይ ክልል የአላማጣ ከተማ ነዋሪው አቶ ጌታነህ ካሳ እንደተናገሩት ከዓመት በፊት አላማጣ አካባቢ የፀጥታ ችግር አጋጥሞ እያለ ከተፈጠረ መስተጓጎል በስተቀር እንቅስቃሴ የሚያስቆም ሁኔታ አልታዘቡም፡፡

‹‹እኔ እንደማውቀው የተዘጋ መንገድ የለም፤ ወደ ወልድያም ሆነ ቆቦ መኪኖች ይመላለሳሉ፤ የአላማጣና የቆቦ፣ ወልድያ ሕዝብ አንድ ነው ያሉት አቶ ጌታነህ እኔ መንገድ ተዘግቷል የሚለውን ስጠየቅ መስማቴ ነው›› ብለዋል፡፡

አቶ መርጊያው ተካ የተባሉ የቆቦ ከተማ ነዋሪ ደግሞ ‹‹ከመቀሌ-አላማጣ-ቆቦ -ደሴ -አዲስ አበባ የተዘጋ መንገድ የለም ያሉ ሲሆን ከዓመት በፊት አላማጣ በተነሳ ችግር ለቀናት ከነበረ ግርግር በስተቀር መንገዱም ግንኙነታችንም ሠላማዊ ነው፤ ማንኛውም ተሽከርካሪ እያለፈ ነው›› ብለዋል፡፡

የአላማጣና የራያ አካባቢ ኅብረተሰብ አንድነቱ የጠነከረና በደስታና በሐዘን የማይለያይ መሆኑን የተናገሩት አቶ መርጊያው ‹‹በፖለቲከኞች መካከል ችግር እንዳለ እንሰማለን፤ በኛ መካከል ግን ኮሽታም የለብን፤ አብረን ኑሯችንን እየመራን ነው›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የተሽከርካሪ እንቅስቃሴ አለመቆሙንና ከየመናኸሪያዎቹ የተለመዱ ስምሪቶች መኖራቸውንም ግለሰቡ አመልክተዋል፡፡

ከአላማጣ ከተማ የመንገድ ትራፊክ ሥራ ክፍል የተገኘው መረጃ ደግሞ ‹‹የአላማጣ-ቆቦ-ወልድያ መንገድ ዝግ አይደለም፤ መለስተኛና አነስተኛ የሕዝብ ማመላለሻዎች በአላማጣ-ቆቦ-ወልድያ- ደሴ ይንቀሳቀሳሉ፡፡ የሚል ነው፡፡

ከባድ መኪኖች ግን ከዓመት በፊት አጋጥሞ በነበረ የፀጥታ ችግር ምክንያት ስጋት ስላላቸው በአላማጣ-ቆቦ አድርገው ወልድያ ሳይገቡ በአፋር በኩል ነው ወደ አዲስ አበባ የሚሄዱ ቢሆንም መንገዱ ግን መዘጋቱን አልሰማሁም›› ሲል አስታውቋል፡፡