አባይ ሚዲያ ዜና – ጥቅምት 5፣ 2012

የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ለሰባት ቀናት ሲያካሄድ የነበረውን ስብሰባ በማጠናቀቅ መግለጫ ያወጣ ሲሆን የተለመደ የአንድነትና የህብረት አካሄድን በመጻረር የኢህአዴግ መዋሃድ እርምጃን በተመለከተ ያለውን አቋም አንጸባርቋል።

የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዲሞክራሲያዊ ግንባር -ኢህአዴግ መስራች እና ዋነኛ አባል የሆነው ህወሓት ፤ የኢህአዴግ የውህደት እንቅስቃሴን አጥብቆ ኮንኗል።

ህወሓት በመግለጫው “ከኢህዴግ ርዕዮተ ዓለም እና መተዳደሪያ ደንብ ውጪ አንድ ውህድ ፓርቲ ለመመስረት እየተደረገ ያለው ሩጫ ሕገ-ወጥ ነው” ብሏል።

ህወሓት “እሳት እና ጭድ የሆኑ ፓርቲዎች በውስጥ የተሸከመው ግንባር፤ አይደለም ውህደት ፓርቲ በግንባርነት አብሮ የሚያቆይ የጋራ አስተሳሰብ እንኳን የላቸውም” ሲል ጠንከር ያለ እገላለጽን በመግለጫው ላይ አስፍሯል።

መግለጫውን ተከትሎ በትግራይ ክልል የህወኃት ተቃዋሚና ተፎካካሪ የሆነው ትዴት ፓርቲ ሊቀመንበር ዶ/ር አረጋዊ በርሄ ለአባይ ሚዲያ እንደገለጹት መግለጫው ህወሓት በግልጽ ከአዲሱ የኢህአዴግ አካሄድ ያፈነገጠ መሆኑን የሚያሳይ ነው ሲሉ ነግረውናል፡፡

ዶ/ር አረጋዊ እንዳሉት መግለጫው ያለ ምክናየት የወጣና የተለመደ የተቃውሞ አባዜ የተያበት እንጂ ህወሓት ስልጣን ላይ እያለ ካልተዋሃድን ብሎ ሲወተውት እንደነበር አይረሳም ብለዋል፡፡