አባይ ሚዲያ ዜና – ጥቅምት 5፣ 2012

በየአመቱ ጥቅምት ወር የሚካሄደው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የመንበረ ፓትሪያርክ አጠቃላይ ሰበካ 38ኛ ጉባኤ መካሄድ የጀመረ ሲሆን ጉባኤው ከጥቅምት 5 እስከ 8 ቀን 2012 ዓ.ም ድረስ የሚካሄድ ነው።

ጉባኤውን በንግግር የከፈቱት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፥ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ስለሕዝቦች ሁለንተናዊ ደኅንነት መጸለይ፣ ማስተማርና መምከር ከእግዚአብሔር የተቀበለችው ዓቢይ ተልእኮ ነው ብለዋል።

ይህም ዘወትር የምታከናውነው ተቀዳሚ ተግባርዋ ቢሆንም፥ በተለይም አሁን ባለንበት ወቅት በከፍተኛ ደረጃ በጸሎትና በማስተማር፣ በመምከርና በማስታረቅ ተግታ የምትሠራበት ጊዜ እንደሆነ እንገነዘባለን ነው ያሉት።

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ዛሬ ሀገሪቱ በተስፋና በሥጋት መካከል ተወጥራ ያለችበት እንዲሁም የቤተ ክርስቲያን ማእከላዊ መዋቅር እየተፈተነ የሚገኝበት አሳሳቢ ወቅት ነው በማለት ተናግረዋል።

በዚህ ፈታኝ ወቅት ቤተ ክርስቲያን ትዕግሥት ያልተለየው ጥበብና ብልሃት ተጠቅማ ልጆቿን ወደ አንድነት ማሰባሰብ ከምንም በላይ ተቀዳሚ ተግባር አድርጋ መውሰድ ይጠበቅበታልም ብለዋል።

ቤተ ክርስቲያን ከእግዚአብሔር የተሰጣት የማስታረቅና የማስተማር፣ የመምከርና የማሰባሰብ ኃላፊነት የምታከናውነው አንዱን በማራቅ፣ ሌላውን በማቅረብ አንዱን በመደገፍ ሌላውን በመንቀፍ ሳይሆን ሁሉም ልጆቿ ናቸውና በእኩልነት፣ በአንድነት፣ በፍቅርና በገለልተኝነት መሆን እንዳለበት አሳስበዋል።

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ አክለውም ቤተ ክርስቲያኗ ከፖለቲካ ንክኪ ፍጹም ነጻ ሆና ሥራዋን እንድትቀጥል ማድረግ የሁሉም የቤተ ክርስቲያን አመራሮች፣ አገልጋዮችና ሠራተኞች የውዴታ ግዴታ ነው ብለዋል፡፡

በጉባኤው ከ82 በላይ ሀገረ ስብከቶች የስራ አፈፃጸም አቅድ ቀርቦ ውይይት እንደሚደረግበት ነው የተነገረው።

በዋነኝነት 2011 ዓ.ም በልማት፣ ኢኮኖሚና ማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ የተሰሩ ስራዎች እና በ2012 በሚሰሩ አበይት ተግባራት ዙሪያ የሚመከርበት ጉባኤ ነው ተብሏል።