አባይ ሚዲያ ዜና – ጥቅምት 5፣ 2012

በባህር ዳርና አዲስ አበባ ከተሞች ውስጥ በተቀራራቢ ሰዓታት በአሰቃቂ ሁኔታ በተገደሉት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ምክንያት ተጠርጥረው ለሦስት ወራት ያህል ታስረው የነበሩት ‹‹እነ ብርጋዴር ጄኔራል ተፈራ ማሞ፣ እንዲለቀቁ የተደረጉበት ምክንያት የተጠረጠሩበት ጉዳይ ዋስትና ስለማያስከለክል ነውን?›› የሚል ጥያቄ እየተነሳ ነው፡፡

ተጠርጣሪዎቹ የክልሉ ልዩ ኃይል አዛዥ የነበሩት ብርጋዴር ጄኔራል ተፈራ ማሞ፣ ኮሎኔል አለበል አማረና ኮሎኔል ባምላክ ዓባይ፣ ጥቅምት 3 ቀን 2012 ዓ.ም. እያንዳንዳቸውን በ10,000 ብር ዋስትና መለቀቃቸውን አስመልክቶ፣ የሕግ ባለሙያዎች የተጠረጠሩበት ወንጀል ዋስትና የማይከለክል ከሆነ፣ ‹‹ለምን ይህንን ያህል ጊዜ እንዲታሰሩ ተደረገ?›› በማለት ጠይቀዋል፡፡

የሕግ ባለሙያው አቶ አብዱ መሐመድ እንደገለጹት፣ ተጠርጣሪዎቹ በእስር ያሳለፉት ጊዜ በጣም ብዙ ሲሆን መርማሪ ፖሊስና ዓቃቤ ሕግ ተጠርጠሪዎቹ የተጠረጠሩበት የወንጀል ድርጊት ውስጥ ታሳታፊ መሆናቸውን የሚያመላክት ተጨባጭ ማስረጃ ለመፈለግ፣ ቢበዛ ቢበዛ ከሁለት ቀጠሮ በላይ መሄድ አይገባቸውም ነበር ብለዋል፡፡

ማስረጃ ባይገኝ እንኳ፣ ‹‹አሁን እንዳደረጉት›› የተጠረጠሩበት ጉዳይ ዋስትና እንደማያስከለክል ከተረዱ፣ የዋስትና ሁኔታ ላይ በመከራከር በበቂ ዋስትና እንዲለቀቁ ማድረግ ይችሉ እንደነበር አስረድተዋል፡፡

ተጠርጣሪን ለሦስት ወራት አስሮ፣ ‹የተጠረጠሩበት ጉዳይ ዋስትና ስለማያስከለክል በዋስ ቢለቀቁ አልቃወምም፤›› ማለት ተገቢ አለመሆኑን አክለዋል፡፡
ዓቃቤ ሕግ አንድን ተጠርጣሪ አስሮና ወንጀል ፈልጎ ማስቀጣት ብቻ ሳይሆን፣ ተጠርጣሪው ነፃ መሆኑን የማጣራት ኃላፊነትም እንዳለበት የጠቆሙት የሕግ ባለሙያው፣ ያልተሠራ ወንጀል ወይም ማስረጃ ለመፈላለግ ሰዎችን በእስር ማቆየት፣ ሕገ መንግሥታዊና ተፈጥሯዊ የመዘዋወር መብትን ከማጣስ ባለፈ፣ በሕግ የሚያስጠይቅ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡