አባይ ሚዲያ ዜና – ጥቅምት 5፣ 2012

የኢፌዴሪ ገቢዎች ሚኒስቴር በጉምሩክ ኮሚሽን የጂግጂጋ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት የህግ ማሰከበር ኃላፊ አቶ አህመድ መሐመድ እና ምክትል ኃላፊያቸው አቶ አብዱልዋህድ አብዱላህ ከህገ ወጥ የኮንትረባንድ ዝውውር ጋር በተያያዘ በከባድ የሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር መዋላቸው ይታወሳል፡፡

1ኛ ተከሳሽ አቶ አህመድ መሐመድ እና 2ኛ ተከሳሽ አቶ አብዱልዋህድ አብዱላህ በጉምሩክ ኮሚሽን የጂግጂጋ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት የህግ ማሰከበር ኃላፊ እና ምክትል ኃላፊያቸው ሆነው ሲሰሩ በነበረበት ወቅት የኮንትሮባንድን በሕጋዊ መንገድ ወደ ተግባር ለማስገባት በመሞከር የንግድ እንቅስቃሴን በሚጎዳ፣በህዝብና በመንግስት ላይ የሚደርሰውን ጉዳት እያወቁ የግል ጥቅምን ለማግኘት ሲባል ሚያዚያ 8 ቀን 2010 ዓ.ም በሱማሌ ክልል አሩዋ ወረዳ ከባድ ሙስና ወንጅል በመፈጸም ተይዘው ፍርድ ቤት መቅረባቸውን የክስ መዝገቡ ያስረዳል፡፡

ተከሳሾች አቶ አህመድ ጣህር ከሚባል ግለስብ ጋር በመመሳጠር አጠቃላይ የዋጋ ግምቱ ከ1 ሚሊዩን በላይ የሆነ ብዛቱ 2000 ሺህ ካርቶን ህገ ወጥ ሲጋራ በሁለት ዩዲ መኪና ወደ አገር ውስጥ ሲጋባ ሕጋዊና ተገቢ ርምጃ መውሰድ ሲገባቸው የተሰጣቸውን ሥልጣንና ኃላፊነት ወደ ጎን በመተው ህገ ወጥ የኮንትሮባንድ ንግድ እንዲስፋፋ በማድረግ 1ኛ ተከሳሽ አቶ አህመድ መሐመድ 1.7 ሚሊዩን ብር ግቦ ተቀብሎ ሲጋራው እንዲያልፍ አድርጓል፡፡

2ኛ ተከሳሽ አቶ አብዱልዋህድ አብዱላህ በኮንትሮባንድ የገባውን ሲጋራ መያዝ ሲገባቸው እያዩ ዝም በማለት ስልጣናቸውን አላግባብ በመጠቀም በህዝብና በመንግስት ላይ ጉዳት የሚያደርስ ከባድ የሙስና ወንጀል በመፈፀም ተከሰዋል፡፡

በዛሬው ዕላት ተከሳሾች በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 18ኛ ወንጀል ችሎት ቀርበው የዐቃቤ ሕግ ክስ ዝርዘር ተነቦላቸዋል፡፡