አባይ ሚዲያ ዜና – ጥቅምት 5፣ 2012

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሰላም እየራቃትና ግጭቶች በተደጋጋሚ እየተከሰቱባት የምትገኘው ድሬዳዋ ትላናትም ወጣቶቿ በመከላከያና በፖሊስ ሀይል መታሰራቸውን የአባይ ሚዲያ ምንጮች አረጋግጠዋል፡፡

የመረጃ ምንጫችን በስልክ እንደነገሩን እሁድ ዕለት ለጠቅላይ ሚኒስተር ዐቢይ አህመድ ድጋፍ የደስታ መግለጫ በተካሄደ ሰልፍ ላይ የተሰሙ ጸያፍና ተገቢ ያልሆኑ ድምጾች የከተማዋን ወጣቶች በማንነት ላይ ባነጣጠረ ስደብ ግጭት ውስጥ የከተተበት አጋጣሚ የተፈጠረ ሲሆን በነበረው ጸብ አጫሪ እንቅስቃሴ ምክናየት ግጭት ተፈጥሮ መከላከያ ለመግባት ተገዶ እንደነበር ገልጸዋል፡፡

በተለይም በጊዜው የከተማዋ ወጣቶች ራሳቸውንና አካባቢያቸውን ከጥቃት ለመከላከል ባደረጉት አጸፋዊ እንቅስቃሴ ከሰልፈኞቹ አልፈው ከመከላከያና ከፖሊስ ጋር አለመግባባት ውስጥ ገብተው ስለነበር ነገሩ ወደ አልተፈለገ መንገድ እንዳመራ የመረጃ ምንጫችን አክለው ነግረውናል፡፡

ፖሊስ ህግ በማስከበር ሽፋን ህገወጥ አካሄድ እተከተለ ነው ያሉት ምንጫችን ነገሮች ከተረጋጉ በኋላም ፖሊስ በየቤቱ እየተዘዋወረ ወጣቶችን እያፈሰ እንደሆነና ወጣቶች በፖሊስ ከተወሰዱ በኋላም በህጋዊ መንገድ ለፍርድ እየቀረቡ አይደለም ብለዋል፡፡

በጉዳዩ ላይ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ወደ ከተማዋ ፖሊስ ያደረግነው የስልክ ሙከራ ለጊዜው አልተሳካም፡፡