አባይ ሚዲያ ጥቅምት 9፣2012

በብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት የሚቀጠሩም ሆነ የሚመደቡ ሠራተኞች በተቋም ላይ የደኅንነት ሥጋት ወይም አደጋ አለማስከተላቸው ሲታመነበት ብቻ፣  እንዲቀጠሩ ወይም እንዲመደቡ የሚያስገድድና ይህንንም ተግባራዊ ለማድረግ “በፖሊግራፍ” ቴክኖሎጂ የተደገፈ ምርመራ ሊደረግባቸው እንደሚችል ተገለጸ፡፡

ሪፎርሙ ተጠናቆ ተግባራዊ መደረግ ሲጀምር በተቋሙ የሚቀጠሩም ሆነ የሚመደቡ ሠራተኞች ላይ ጥብቅ የደኅንነት ማጣራት ይደረጋልም ተብሏል፡፡

የደኅንነት ማጣራት ሒደቱን ውጤታማ ለማድረግም “የፖሊግራፍ” ምርመራ ጥቅም ላይ እንደሚውል ለማወቅ ተችሏል፡፡

“የፖሊግራፍ” ምርመራ ሐሰተኛ መረጃን ለመለየት የሚረዳ ቴክኖሎጂ ሲሆን፣ በዚህ ምርመራ ውስጥ የሚያልፉ ግለሰቦች ለሚቀርቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ በሚሰጡበት ወቅት የሚስተዋልባቸውን አካላዊና ስሜታዊ ለውጦችን የምርመራ መሣሪያው በመመዝገብና በመተንተን የሰጡት መረጃ ሐሰተኛ መሆን አለመሆኑን ለመለየት የሚረዳ ነው፡፡