አባይ ሚዲያ ጥቅምት 9፣2012

በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ጥሩና አስቸጋሪ ሁኔታዎች ተቀላቅለው የሚገኙ በመሆናቸው በግልጽ መነጋገር ቅድሚያ የሚሰጠው ከመሆኑም ባሻገር፣ ከፖለቲከኞችና ከፖለቲካ በላይ እንደ ቀለበት ሁሉንም ያቆራኘች አገር እንደምትቀድም የሰላም ሚኒስትሯ ተናገሩ፡፡

የሰላም ሚኒስትሯ ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል ፖለቲከኞች በአገር ጉዳይ ላይ ያላቸው ቦታና ሚና እንዳለ ሆኖ፣ ዘላቂ የሆነ መፍትሔ ለማምጣትና ቀጣይነት ያለው ሰላምና የዴሞክራሲ ግንባታ ለማካሄድ፣ ሁሉንም አቆራኝታ የያዘችን አገር መጠበቅ ግድ የሚል መሆኑን  ተናግረዋል፡፡

ለዚህ ደግሞ የድንቅና ረቂቅ ባለቤት የሆኑት ለማንም የማይወግኑ፣ ለማንም የማይቆሙ፣ አገርንና የኢትዮጵያን ሕዝቦች ብቻ የሚወዱ የአገር ሽማግሌዎች ሚና ትልቅና መተኪያ የሌለው የፈውስ መንገድ እንደሚሆኑ እምነታቸው መሆኑን አስምረውበታል፡፡

ኢትዮጵያ አሁን ያለችበት ወቅት ጥሩና አስቸጋሪ ሁኔታዎች ተቀላቅለው የሚገኙበት መሆኑን የጠቆሙት ሚኒስትሯ፣ ሁሉንም ነገር በግልጽ መነጋገር አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

አንዳንዱ ሁሉ ነገር አልጋ በአልጋ እንደሆነ ሲያስብ፣ ሌላው ደግሞ ሁሉም ነገር ጨለማ እንደሆነ ካሰበ ለማቀራረብ አስቸጋሪና አዳጋች እንደሚሆንም አክለዋል፡፡

በማንኛውም የሽግግር ሒደት ውስጥ እንደሚያጋጥመው ተግዳሮት ኢትዮጵያም የተለያዩ ተግዳሮቶች እንዳጋጠሟት የጠቆሙት ወ/ሮ ሙፈሪያት፣ ይኼ ሊስተባበል የማይችል ሀቅ ቢሆንም ድሉንም ሆነ ችግሩን በልክ በልኩ ከማየት አንፃር ትልቅ ጎዶሎ ያለ በመሆኑ፣ ይኼንን ጎዶሎ ለመሙላት ወይም ለመፍታት የአገር ሽማግሌዎችን ያህል ሚና ያለው አካል አለ ብለው እንደማያምኑ አስረድተዋል፡፡

የብሔራዊ የአገር ሽማግሌዎች ምክክር መድረክ ሰብሳቢ ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ እንደገለጹት በቀደመው ጊዜ፣ ዘመን የማይተካው የሃይማኖት አባቶችን፣ የአገር መሪዎችንና አፍላ ወጣቶችን አገሪቱ አጥታለች ሲሉ አስታውሰዋል፡፡