የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት በኢትዮጵያ ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ አስመልክቶ መግለጫ ያወጣ ሲሆን በመግለጫውም የሃገርን ሰላም በማስቀደም ለመረጋጋት መስራት እንደሚገባ አሳስቧል።

ኢትዮጵያ በቅድመ ለውጡም ሆነ ድህረ ለውጡ ጊዜ ብዙ ችግሮችን ማስተናገዷን እና ብዙ ችግሮች መታየታቸውን ያነሳው ምክር ቤቱ፥ አሁንም ወደተረጋጋ ዴሞክራሲ፣ ነጻነት እና እኩልነት እስከሚደረስ ብዙ ችግሮችን ማለፍ ይጠበቃል ነው ያለው።

ችግርም ሆነ ፈተና የህይወት አንድ ቋሚ አካል መሆኑን የአላህ ቃል የሆነው ቅዱስ ቁርአን እንደሚያስተምርም ምክር ቤቱ በመግለጫው አመላክቷል።

ምክር ቤቱ ሀገሪቱ ውስጥ የሚከሰቱ ችግሮች ሁሉንም በጋራ የሚጎዱ፣ ቀውሶች የሁሉንም ዜጋ መስተጋብር የሚፈትኑና ማህበረሰባዊ ትስስሮችን የሚበጥሱ በመሆናቸው አላህ የሰጠን ፀጋ አካል የሆነችው ውድ እናት ሃገራችንን ወደተወሳሰበ የችግር አዘቅት እንዳትገባ መጠንቀቅ ሃይማኖታዊም ዓለማዊም ግዴታ ነው ብሏል፡፡

ቀውስ ሲከሰት፣ ችግር ሲበራከት፣ ግጭት ሲስፋፋ ሁሉም ለማረጋጋት የመጣር ኃላፊነት እንዳለበት በመግለፅም ትኩሳት እንዲበርድ፣ ህይወት ወደመረጋጋት እንዲመለስ መስራት አለብን ነው ያለው በመግለጫው።

ህገ ወጥነት እና ስርዓት አልበኝነት እንዳይሰፍን፣ አላህ ክብር የሰጠው የሰው ልጅ ነፍስ እንዳይጠፋ፣ ፖለቲከኞች ወደስክነት እንዲመጡ ሁላችንም አላህን ልንለምን ይገባል በማለትም አሳስቧል።

አንዳችን ለአንዳችን ችግር በመቆርቆር ትስስራችንን ማጠናገር ይገባል ያለው ምክር ቤቱ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ለእርቅ እና ለስክነት ሊሰሩ እንደሚገባ ጥሪውን አቅርቧል።

ማህበረሰባዊ እና አካላዊ ሰላም ለአንድ ሃገር እጅግ አስፈላጊ መሆኑን በመጥቀስም፥ የሰላም መጥፋት ጉዳት ሃገራዊ በመሆኑ ተስፋፊ ቀውስ ትስስሩን እንዳያዳክም ሁሉም የሰላም ምንጭ የሆነውን አላህን አጥብቀን እንድንለምን፣ ቀውሱን ከሚያሰፉ ማናቸውም ተግባራት መቆጠብ እንደሚገባማ ለመላው ሙስሊም ህብረተሰብ ጥሪውን አስተላልፏል።