እየሆነ ያለው ሁሉ አይደለም እያየነው ለመስማትም ይዘገንናል ኢትዮጵያዊነት ከምናውቀው እና ከኖርንበት ዘመን ውጪ የሆነ ትርክት እስኪመስለን ድረስ ቅጡን ባጣ ጋጠ ወጥነትና በሰው ዘር ታሪክ ፈፅሞ ሊታሰብ የማይችል ጭካኔ እና በሰው የተመሰሉ ፍጡራን ሃገራችንን የወረሩበት ሁኔታ ያለ እስኪመስለን ድረስ በፍፁም ጥላቻ የተወሩ የዘመኑ ክፉ መንፈስ የተጠናወታቸው ቄሮ ነን ባይ ነገር ግን ቄሮ ትርጉሙ ያልገባቸው በአውሬው መንፈስ ጃዋር መሐመድ የሚመሩ ነገር ግን እናምነዋለን የሚሉትን ፈጣሪ ትዕዛዝ ፈፅሞ የተፃረሩ እርኩሳን በሃገራችን እና በኢትዮጵያውያን እያደረሱት ያለው መጠነ ሰፊ የደም ማፍሰስ ጥማት ህመሙ ኢትዮጵያዊያንን ያሳመመ ድርጊት ከሆነ ውሎ አድሯል ነገር ግን ይህ ሰቆቃ ያላመመው ቢኖር አራት ኪሎ የተቀመጠው መንግሥት ብቻ ይመስለኛል ። የሄን የምለው የመንግሥት አካል ህመሙ ተሰምቶት አንድም ቀን ሲያቃስት ወይም ሲቃትት ሰምቼው ስለማላውቅ ነው ይህም ማለት ዱላው በስብስቡ አካል በአንዱም ላይ ባለማረፉ ነው ።
ሃገራችን ሃብት ንብረቷ ሲዘረፍ ፣ ህፃናት እና አረጋውያን በክረምት ቤታቸው በላያቸው ላይ ሲፈርስ ፣ ዜጎች በጠራራ ፀሃይ በቆንጨራ ገላቸው ሲበለት ሊያውም በአዋጅ ነገ እርምጃ እንወስድባችኋለን እየተባሉና ዛቻውም ሢፈፀምባቸው ማየቱን መንግሥታችን ተለማምዶት የለበጣ መግለጫ እና የይስሙላ ዛቻ መሰንዘሩን ሲቀጥልበት በሌላ ጎን ተደራጅተን እራሳችንን እንከላከል ያሉ ወጣቶች ወይም ዜጎች ግን በተፃራሪው ከመንግሥት ፖሊስ / ሰራዊት እስራት እና ግርፋት ሲሰነዘርባቸው ይኸው ድፍን አመት አለፈን ። ድሮ ድሮ ባሎቻቸው ወይም ወጣት ልጆቻቸው ለሃገራቸው ሲዘምቱ እልል ብለው ከመሸኘት ባለፈ አልቅሰው የማያውቁት እናቶች ይቅርና እኛም ወንዶቹ ፅንፈኞች በዜጎች ላይ የሚያደርሱትን ጭፍጨፋ በማየት የመጀመሪያዎቹ አልቃሻዎች ሆነናል ፣ ሕፃናት ዘግናኝ ድርጊቶችን እያዩ ያለቅሳሉ ፣ እናቶች ስለ ልጆቻቸው ደም መፍሰስ ያለቅሳሉ ፣ የሃገር ሽማግሌዎች ያነባሉ ፣ የሃይማኖት አባቶችም እንባ ይወርዳል ። ታዲያ ይህን እንባ መንግሥት እንዴት ሊታደገው አልቻለም ወይም አልፈለገም ከሁሉ የሚገርመው ለዚህ ሁሉ እልቂት ከበሮ መቺዎች ወይም የጭፍጨፋው ፊሽካ ነፊዎች ሁሌም ከመንግሥት ጋር በገበታም ሆነ በሌሎች ሆይ ሆይታዎች ላይ አብረው ይታያሉ ። ለዚህም ይመስለኛል አንዳንዶች ኢትዮጵያ ለሽብርተኛ መጠለያ የሰጠች ብቸኛዋ ሃገር እያሉ የሚተቹት ።
የመንግሥታችን ትዕግሥት እስከምን ድረስ ነው ትዕግስትም እኮ ገደብ ሊኖረው ይገባል በመለሳለስ እና ስሜታዊነትን ያዝ አድርጎ ስለመጪው ዘመን አርቆ በማየት በፍቅር ለማሸነፍም የሚኬድበት መንገድ ደግ ሆኖ ሳለ አሁን ግን እያየነው ያለው ዝምታው እራሱ ለፅንፈኞች የልብ ልብ የሰጠና ተረኝነቱ እንደማይቀር በግልፅ እየነገረን ነው ።
አፄ ሚኒሊክ ጡት ቆረጡ ብለው ዋይታ ያበዙ ፅንፈኞች በተራቸው የእናቶች ጡት እየቆረጡ ፣ በአደባባይ በተለያዩ ቦታዎች በዱላ እና በድንጋይ ዜጎችን ጨፍጭፈው ሲገሉ ሰምተን በማናውቀው ሁኔታ የገዛ ወገናቸውን ዘቅዝቀው ሲሰቅሉ በግልፅ በአደባባይ እያየን ነው ያለነው ።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ አባቶች እና ምዕመናን በሃይማኖታቸው ብቻ ታድነው ሲገደሉ እና ከቤተ እግዚአብሔር ጋር በእሳት ሲቃጠሉ ማየት የዘወትር ተግባር ሆኗል የሚሆነውን ሁሉ ወያኔና ጽንፈኛ የኦሮሞ ድርጅቶች በመናበብ እየሰሩት ያለ ደባ ለመሆኑ ምንም ምስክር አያስፈልገውም ።
ለዚህም ነው ማነው የእልቂታችን አበረታች ወይም ከጀርባ ሆኖ የትልቁ ከበሮ ደብዳቢ አሊያም የህዝብ እንባ አዳሽ የህፃናት ሰቆቃ የሚያመው ብለን ብንል በዚህ ዘመን ከፈጣሪው በስተቀር ማን ይኖረዋል ? መተሻሸቱ በዝቶ ዽርጊቶች ህመማቸው ሲበረታ እና ንቀቱ ሲጨምር ሰቆቃው ወደ አራት ኪሎ የማይመጣበት ምክንያት የለም ፣ እሳት ተነስቶ እኛ ውሃ ውስጥ ነን ምነም አይነካም ብለው ሲጎርሩ የነበሩት እንቁራሪቶች በመንደርተኛው እየተጨለፉ ወደ እሳቱ የተወረወሩበት ታሪክ እውን አራት ኪሎ የማይገባበት ምክንያት ይኖራል ?
እንግዲህ ይሄ ሁሉ እየሆነ ያለው ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ለማድረግ ጥቂት ወራት በቀሯት በዚህችው ሰቆቃ በሚፈፀምባት ሃገራችን ነው ። ተፎካካሪ ወይም ተለጣፊ ፓርቲዎችስ ለምርጫ ከምታደርጉት ቅስቀሳ በተጓዳኝ ፅንፈኛ ገዳዮችን ለማውገዝ ምን ይሆን አንደበታችሁን የለጎመው ? መንግሥትንስ ለመውቀስ ምን ይሆን ያስፈራችሁ? ሁሉም ነገር ያማል ይበቃኛል ።
27 ኦክቶበር 2019
ስቶክሆልም