አባይ ሚዲያ ዜና- ጥቅምት 19፣2012

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ አፈፃፀም ላይ የተቋረጡ ውይይቶችን ለመቀጠል ግብፅ ፣ ኢትዮጵያ እና ሱዳን ጥቅምት 26 ቀን 2012 ዓ.ም በአሜሪካ ዋሽንግተን ከተማ እንደሚገናኙ የግብጹ አህራም ኦን ላይን ዘግቧል፡፡

የዋሽንግተኑ ስብሰባ ግብጽ በህዳሴው ግድብ ዙሪያ አሜሪካ በአደራዳሪነት እንድትሳተፍ በቀረበ ጥያቄ መሰረት መዘጋጀቱ ተገልጿል።

የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሚ ሽኩሪ ከጀርመን አቻቸው ጋር በሰጡት መግለጫ እንዳሉት ግብጽ ከሶስት ወራት በፊት ለትራምፕ አስተዳደር ባቀረበው የአሸማግሉን ጥያቄ መሰረት እንደሆነ አሳውቀዋል፡፡

ሳሚ ሽኩሪ የሽምግልና ሀሳቡ የመልካም ፍላጎት ማረጋገጫ እንደሆነ ግብጽ ትረዳለች ያሉ ሲሆን ግብፅ በዲፕሎማሲያዊ እና በሰላማዊ መንገድ ሁሉንም ጉዳዮች ለመተባበር እና አለመግባባቶችን ለመፍታት እንደምትሞክርም ተናግረዋል ፡፡

ይሁን እንጂ ኢትዮጵያም ሆነ ሱዳን በአሜሪካ አሸማጋይነት በሚደረገው ውይይት ስለመገኘታቸው እስካሁን በግልጽ ያሉት ነገር የለም።

የሽምግልናው ሀሳብ በሶስቱ ሀገራት የተፈረመውን የ2015 መርሆዎች መሰረት ያደረገ መሆኑንም ሽኩሪ ተናግረዋል ፡፡

በመርሁ መሰረት ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት በክርክር ወይም በድርድር ለመፍታት ካልቻሉ የሌላ ገለልተኛ አካል ሽምግልናን መጠየቅ ይችላሉ ፡፡

ግብጽ በ2017 በግድቡ ዙሪያ የዓለም ባንክ እንዲያደራድር ጠይቃ የነበረ ቢሆንም በኢትዮጵያ ተቀባይነት አላገኘም ነበር፡፡

በጎዳዩ ላይ ሀሳብ እንዲሰጠው የኢትዮጲያ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ ነብያት ጌታቸው ግብጽ ስላለችው የዋሸንግተን ድርድር ጉዳይ “እስካሁን የደረሰን መረጃ የለም” ብለዋል፡፡

ግብፅ የግድቡን የመሙላት ሂደት ሰባት አመት እንዲሆን ስትል ብትጠይቅም የኢትዮጲያ መንግስት ግን ግድቡን በሶስት አመት ውስጥ ለመሙላት ማቀዱን አስታውቋል፡፡