አባይ ሚዲያ ዜና- ጥቅምት 19፣2012

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጥቅምት 03/2012 ከ30,000 ለሚልቁ ሰራተኞቹ በላከው የውስጥ ማስታወሻ የደንበኛ አገልግሎት የሚሰጡ የድርጅቱ ሠራተኞች በሥራ ሰዓት የስልክ ጥሪን ጨምሮ የማህበራዊ ሚድያ እና ሌሎች የሞባይል ስልክ አገልግሎቶችን እንዳይጠቀሙ መከልከሉን አዲስ ማለዳ ጋዜጣ ዘግቧል።

ጋዜጣው አገኘሁት ባለው መረጃ በሲስተም መጨናነቅ ምክንያትና የኤቲኤም ማሽኖች በአግባቡ ባለመሥራታቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ የደንበኞቹ ቅሬታ እየጠነከረ የመጣበት ባንኩ፣ በስትራቴጂክ እና ኢኖቬሽን ክፍሉ አማካኝነት አጠናሁ ባለው የዳሰሳ ጥናት መሠረት፤ የደንበኞች አገልግሎት አሰጣጥ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሽቆለቆለ መጥቶ የከፋ ደረጃ ላይ ደርሷል።

ለዚህም አንኳር ተብለው ከተቀመጡ ምክንያቶች መካከል የደንበኞች አገልግሎት ሰጪ ሠራተኞች የሞባይል ስልክ አጠቃቀም ሆኖ በመገኘቱ በውስጥ እርምጃው እንዳስፈለገ የውስጥ ማስታወሻው ላይ መጠቀሱን በማንሳት አዲስ ማለዳ ዘግቧል።