አባይ ሚዲያ ዜና- ጥቅምት 19፣2012

ከጥቅምት 12 ጀምሮ በነበሩ ጥቃትና ግጭቶች በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የተሳተፉ ለሕግ እንዲቀርቡ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ጠየቀ፡፡

እስከ አሁን ባለው መረጃ ከ70 – 80 የሚደርሱ ሰዎች ሕይወት ጠፍቷል ያለው ኮሚሽኑ አስሩ ከፀጥታ ኃይሎች ጋር በተፈጠረ ግጭት በጥይት ተመተው መሞታቸውን ገልጿል፡፡

አብዛኛዎቹ ግን ‹‹እጅግ አሰቃቂ በሆነ መንገድ በግፍ እና ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ በዱላ በድንጋይ እና በስለት ተደብድበው እንዲሁም በእሳት ተቃጥለው ተገድለዋል›› ብሏል፡፡

መንግሥት አጥፊዎችን ሁሉ ሕግ ፊት አቀርባለሁ ማለቱን ያስታወሰው ኮሚሽኑ ቃሉ በስልታዊ የምርመራ ሥራ እና በሕጋዊ ሥርዓት በአፋጣኝ በሥራ ላይ እንዲውልም ጠይቋል፡፡