አባይ ሚዲያ ዜና- ጥቅምት 19፣2012

የቀድሞው ሶማሌ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ አብዲ መሐመድ ኡመር /አብዲ ኢሌ/ በሰጡት የእምነት ክህደት ቃል “ክልሉን በጥሩ ሁኔታ ከማስተዳደር ውጪ ወንጀል አልፈጸምኩም፤ ጥፋተኛም አይደለሁም” ብለዋል፡፡

የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ የወንጀል ችሎት የአቶ አብዲ መሐመድ ኡመርን የእምነት ክህደት ቃል ዛሬ ተቀብሏል፡፡

በሌላ በኩል በአብዲ መሐመድ ኡመር የክስ መዝገብ እስካሁን ያልቀረቡ ሰባት ተከሳሾች የጋዜጣ ጥሪ እንዲደረግላቸውና ውጤቱ ለህዳር 22/2012 ዓ.ም እንዲቀርቡ ችሎቱ ትዕዛዝ መስጠቱን ዋልታ ኢንፎ ዘግቧል፡፡

በተጨማሪም በቁጥጥር ስር ካልዋሉ ተከሳሾች ጋር በተያያዘ የፍትህ መዛባት እየደረሰባቸው መሆኑን ከጠበቆችና ከተከሳሾች ለፍርድ ቤቱ አቤቱታ ቀርቧል፡፡

ፍርድ ቤቱ የተፈጠረው መጓተት ባሉ የተንዛዙ አሰራሮች ጋር በተያያዘ በመሆኑ ወደፊት በተፋጠነ መልኩ ፍትህ የሚሰጥበትን ሁኔታ እንደሚያመቻች አስረድቷል፡፡