የሕሊና ሰለባ የተፈጸመበት ወጣት ለሕግ አይገዛም (በየሺወርቅ ወንድሜነህ)

እንዴት “ለወገኔ እቆረቆራለሁ” የሚል የፖለቲካ ድርጅት “ወገኔ” ለሚለው ወጣት ትውልድ ከሰው በታች የሚያደርግ ድርጊት እንዲፈጽም መመሪያ ይሰጣል?

እንዴት “ወገኔ” የሚለውን ታዳጊ ትውልድ፤ ያለፉ ትውልዶችን ዘመን ከሚመለከትና ለዚያውም ብዙ ጉድለቶች ካለው ትርክት የተቀመመ የጥላቻና የቂም-በቀል መርዝ አጠጥቶ ከሰው በታች የሚያደርገውን ድርጊት እንዲፈጽም ይልካል?

በታዳጊ የኦሮሞ ወጣት ወገኖቻቸው እጅ በጭካኔ የሞቱት ንጹሃን ዜጎች ብቻ ሳይሆኑ መስዋእቶቹ፤ ራሳቸው ወንጀሉን የፈጸሙት ወጣቶችም በመሪዎቻቸው የሕሊና ሰለባ ወንጀል ተፈጽሞባቸዋል። ሕሊናው የተሰለበ ወጣት ትውልድ፤ እልቂትና ሽብር ከማስከተሉም ሌላ ለአገር መፍረስም አስተዋጽኦ ሊያደርግ ይችላል፤ ለዚህም በርካታ የቅርብ ጊዜ የታሪክ ምስክሮች አሉ። በሃይማኖትም ሆነ በጎሳ የማይለያዩ ሕዝቦች እርስ በርሳቸው በመገዳደል አገራቸውን አፈራርሰው፤ የህልውናቸውን ጉዳይ ለውጭ ኃይሎች አሳልፈው የሰጡ ጥቂቶች አይደሉም። እንደምሳሌ ኢራቅን፣ አፍጋኒስታንን፤ ሶሪያንና የመንን መጥቀስ ይቻላል።

ከዚህ አንዴ ከሆነ በቀላሉ ወደኋላ ከማይቀለበስ መጥፎ አደጋ ለመዳን፤ እኛ ኢትዮጵያዊያን ገና እድሉ ጨርሶ አላመለጠንም። ነገር ግን ከማምለጡ በፊት ለመከላልከል ባስቸኳይ መሟላት ያለባቸው የተለያዩ ቅድመ-ሁኔታዎች አሉ። ቅድመ-ሁኔታዎቹን ለመረዳት መሠረት ነው ብዬ የማስበውን ከዚህ በታች ለማብራራት እሞክርና ቅድመ-ሁኔታዎቹን ግን ለሌላ ጊዜ አቆያቸዋለሁ።

በወጣቱ ትውልድ ላይ የሕሊና ሰለባ ተፈጽሞበት፤ ለሕግ የማይገዛ፣ በሰው እኩልነት የማያምንና ሰብአዊ ክብርን ያለምንም የሞራል እቀባ የሚደፍር እንዳይሆን መከላከል የቤተሰብም፣ የጎረቤትም ሆነ የኅብረተሰብ ኃላፊነት ነው።

ነጻ ሕሊናንና ሰፊ ስነ-ልቦናን ሊያዳብሩ በሚችሉ የሕይወት እይታዎች ወይም ፍልስፍናዎች የታነጸና ራሱን ችሎ የሚያስብ፤ ከዚያም የራሱንም ሆነ የሌሎችን ሃሳብ የሚፈትሽ እንጅ የሰማውንና የተሰማውን ሁሉ ፍጹም እውነት ብሎ የማይቀበል ትውልድ ብቻ ነው ከራሱ ጊዜ ጋር በመራመድ፤ ጥቅሙንም መብቱንም በማስከበር እንዲሁም ግዴታና ኃላፊነቱን በመወጣት በሰላምና በብልጽግና ሊኖር የሚችለው። “ዲሞክራሲ፣ ፍትህ፣ እኩልነት፣ ኅብረትና መደጋገፍ” የሚባሉትን ባህሪያት በትክክል ለመገንዘብና በሥራ ለመተርጎምም ነጻ ሕሊና፣ ሰፊ ልቦና እንዲሁም ራስ ችሎ ማሰብን ይጠይቃል። ታዲያ ምን ያህል ነው የኢትዮጵያ የፖለቲካ መሪዎች በዚህ አይነት አመለካከት የታነጸ መሠረት ያላቸው? ምን ያህልስ ነው “እንወድሃለን” የሚሉትን ወጣት ወደዚህ የሚመሩት? ወይስ ድህነቱንና እንግልቱን ተጠቅመው ለጊዜያዊ የሥልጣን ግባቸው የሚገለገሉበት መንጋ ብቻ አድረገው ነው የሚያዩት?

ይሄ ጥያቄዬ በድርጅት ፖለቲካ እየተመራ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ የብዙ ንጹሃን ዜጎችን ሕይወት ባጠፋውና ሽብር እየፈጠረ ባለው ሁኔታ ይቀስቀስ እንጅ፤ ሁሉም የኢትዮጵያ ፖለቲከኞችን የሚመለከት ነው። ከዚህ ቀደም በሌሎች ክልሎችም ውስጥ ግለሰቦች በማንነታቸው የተነሳ የሞት ወንጀል ተፈጽሞባቸዋል። የአንድንም ሰው ሕይወት ቢሆን ያጠፋ በኃላፊነት ሊጠየቅና ሕግ ፊት ሊቀርብ ይገባዋል። ይሄንን የምለው የድርጊቶቹን ልዩነት ለማሳነስ አይደለም፤ በቅርብ ጊዜ የተከሰተው ወንጀልና የኢትዮጵያዊያንን ተስፋ በሽብርና በጥርጣሬ እየለወጠ ያለው የፖለቲካ ሂደት በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የሚመራው የገዥው ድርጅት ውስጥ ቁልፍ ሥልጣን ባላቸውም ሆነ ያለሥልጣን የሕዝብ መሪ ነን በሚሉ ግለሰቦች መሆኑን አልዘነጋሁም።

ከፊሉ የኔ ትውልድ ሕዝቤ ብሎ ያደገው መላው የኢትዮጵያን ሕዝብ ነው። ሕዝባችን ፍትህና እኩልነት ተረጋግጦለት፣ ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቱ ተከብሮለት፤ የሰላምና የብልጽግና እድል እንዲያገኝና ከድህነትና ከኋላ ቀርነት ተላቅቆ ከጊዜ ጋር በመራመድ በኩራት እንዲኖር የታገሉት በርካታ ኢትዮጵያዊያን በአንድ ላይ በግፍ ተገድለው፤ እንደአያት ቅድመ-አያቶቻቸው አንድነታቸው በፈሰሰው ደማቸው ተደባልቋል። ሆኖም ግን ባለፉት 45 አመታት በተደጋጋሚ የሚሰነዘርባቸው ጥቃት አንዱ ከሌላው እየባሰ መጥቷል። ዛሬ ታዲያ ጭንቅላታቸውን በምስማር በመብሳትና አንገታቸውን በቆንጨራ በመቁረጥ ከሚፈስሰው ደማቸው ጋር ኦሮምኛ ተናጋሪውን፣ የሞቱለትን ሕዝባቸውን ከውስጣቸው ለማውጣት የሚደረገው ጥቃት ከሁሉም የባሰ ሆኖ ይሰማል። ያማራው፣ የዶርዜው፣ የጉራጌው፣ የወላይታው፣ የሶማሌው፣ የአደሬው፣ የሲዳማው… ተወላጅ ደንግጧል። የኦሮሞ ሕዝብ ወጥቶ፤ “አይዞህ አይለያዩንም” ቢለው ይረጋጋ ይሆን?

የወጣቱን ሕሊና ሰልቦ፣ ከሰው በታች የሆነ ድርጊት ውስጥ እንዲሰማራ የሚያደርግ ፖለቲካ በሩቁም ይሁን በቅርቡ ያገሮች ታሪክ ውስጥ ለሕዝብ የሚጠቅም ትርፍ አሳይቶ አያውቅም። ይሄንን ቆም ብሎ የማየትና የማሰላሰል እድሉ ገና ጨርሶ አላመለጠምና፤ ሕዝባቸውን የሚወዱ የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች ሁሉ ለሥልጣን የሚያደርጉትን ሩጫ ለጊዜው አቁመው የተከሰቱትን ችግሮች በጋራ በመወያየት ቅደም ተከተል ያለው መፍትሔ እንዲፈልጉ በትህትና እጠይቃለሁ። ይህ ከሁሉም ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር ነው ብዬ ስለማምን ኢትዮጵያዊያን በያለንበት ግፊት ማድረግ ይገባናል።