አባይ ሚዲያ ዜና- ጥቅምት 21፣2012

ትናንት ከባሕር ዳር ወደ መርጡለ ማርያም መንገደኞችን አሳፍሮ ሲጓዝ የነበረ የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪ መገልበጡንና የ15 ሰዎች ሕይወት ማለፉን በአባይ ማለዳ መረጃችን ዘግበን ነበር፡፡

ነገር ግን ትናንት በደረሰው የትራፊክ አደጋ የሟቾች ቁጥር 17 መሆኑን ፖሊስ አስታወቋል፡፡

ዛሬ ጠዋት የጎንጂ ቆለላ ወረዳ ፖሊስ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ኢንስፔክተር ዘለቀ ዓለማየሁ ለአብመድ እንደተናገሩት በአደጋው የ12 ወንዶችና 5 ሴቶች ሕይወት አልፏል፤ 7 ወንዶችና 2 ሴቶች ከባድ እንዲሁም 12 ወንዶችና 8 ሴቶች ቀላል የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡

ሕይወታቸው ካለፉት መካከል አንድ ወንድ እና አንዲት ሴት ማንነታቸውን የሚገልጽ ማስረጃ ይዘው ባለመገኘታቸው አስከሬናቸውን ለቤተሰብ መስጠት ባለመቻሉ በገረገራ ጤና ጣብያ እንደሚገኙም ገልጸዋል፡፡

መኪናው የመጫን አቅሙ እስከ 45 ሰው እንደሆነ ያመለከቱት የጽሕፈት ቤቱ ኃላፊው የተሳፋሪዎች ቁጥር የሟቾችና ተጎጂዎችን ድምር ተወስዶ ሲታይ 46 መሆኑን በመጥቀስ ከአቅም በላይ እንዳልጫነ አስገንዝበዋል፡፡

በአማራ ክልል በዚህ ዓመት የትራፊክ አደጋ እና እያንዳንዱ አደጋ የሚያስከትለው የጉዳት መጠን እየጨመረ መጥቷል፡፡

ምዕራብ ጎጃም ዞን ደምበጫ ዙሪያ ወረዳ መስከረም 12 ቀን 23 ሰዎች፣ ኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ጂሌ ጥሙጋ ወረዳ መስከረም 17 ቀን 9 ሰዎች፣ ዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ሰቆጣ ዙሪያ ወረዳ ጥቅምት 1 ቀን 18 ሰዎች፣ በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ባንጃ ወረዳ ጥቅምት 08 ቀን 10 ሰዎች እና ትናንት ምዕራብ ጎጃም ጎንጂ ቆለላ ወረዳ 17 ሰዎች በድምሩ በአምስት አደጋዎች የ77 ሰዎች ሕይወት አልፏል፤ የበርካቶችም አካል ጎድሏል፡፡

የሚመለከታቸው አካላት አስፈላጊውን የእርምት እርምጃ ለይተው ካልወሰዱ አደጋው አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱን በየጊዜው የሚደርሱ አደጋዎች አመላካች ሆነዋል፡፡