አባይ ሚዲያ ዜና- ጥቀምት 22፣2012

የቀድሞው የኦነግ መሪ የነበሩት የፖለቲካል ሳይንስ ምሁሩ ዶክተር ዲማ ነገዎ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር በነበራቸው ቆይታ ‹‹ኢህአዴግ በመዋሃድ ወጥ ፓርቲ ለመመስረት መንቀሳቀሱን እንደ ጥሩ አጋጣሚ እወስደዋለሁ›› ሲሉ ገለፁ፡፡

ዶክተር ዲማ እንደተናገሩት ኢህአዴግ በውስጡ ያለውን አደረጃጀት የመወሰን የራሱ መብት ነው ያሉ ሲሆን  ሌሎችን የፖለቲካ ድርጅቶች የሚያገባቸው ነገር አይደለም፡፡

ዶክተር ዲማ እንደተናገሩት፤ከዚህ በፊት የነበረው የኢህአዴግ አደረጃጀት አራት አባል ድርጅቶችና አምስት አጋር ድርጅቶች ያሉት ነው፡፡

ይህ አካሄድ በራሱ ልዩነት ያለበት ነው፡፡ አምስቱ አጋርነት እንጂ ሙሉ ተሳታፊ አይደሉም:: አካባቢያቸውን ሊያስተዳድሩ ቢችሉም፤ ኢትዮጵያን ለማስተዳደር ግን አይችሉም ኢትዮጵያን ሊያስተዳድር የሚችል አካል ከአራቱ ብሄራዊ ድርጅቶች ብቻ ነው  ስለዚህም አድልዎ ያለበት አካሄድ እንደሆነ ይገልጻሉ::

ዶክተር ዲማ አክለውም፤‹‹እንዲያም ሆኖ በአራት እህት ድርጅቶቹ መካከልም የስልጣን ተዋረዱ በግልፅ የሚታይ ነው ከላይ በቁንጮነት ሲመራ የነበረው ህወሓት ነው አጋር የተባሉት አምስቱ ግን ከዚህም አሰላለፍ ውጭ ናቸው ስለሆነም ይህ አደረጃጀት በራሱ ችግር ነበረው ብለዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ደግሞ ቆንጮ የነበረው አካል ቀርቶ ኦዲፒ ለመምራት በመፍጨርጨር ላይ ያለ ይመስለኛል እንዲያም ሆኖ የበላይ የበታች በሚል ሐሳብ ውስጥ የመቀጠል ፍላጎት ስለሌላቸው አንድ ወጥ ፓርቲ ለመመስረት እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ ይህን ማድረጋቸውን እኔ እንደ ጥሩ አጋጣሚ ነው የምወስደው ብለዋል፡፡

የኢህአዴግ መዋሃድ ፌዴራሊዝም እንዲከስም አሊያም አሃዳዊነት እንዲመጣ የሚያደርግ ነው የሚሉ አካላት አሉና ምላሽዎ ምንድን ለሚለው ሲመልሱ ‹‹ዴሞክራሲያዊ እስከሆነ ድረስ አሃዳዊም ቢሆን እኔ ችግር የለብኝም፤ዋናው ዴሞክራሲያዊ ነው ወይ? የሚለው ነው፡፡ ››ሲሉ ተናግረዋል፡፡

እንደ እርሳቸው ገለፃ፤እነዚህ ስጋት አለን የሚሉ አካላት የሚያነሱት ኢህአዴግ አሃዳዊ ከሆነ አገሪቱንም ወደዚያው ይወስዳታል ከሚል እሳቤ ነው፡፡

እድሜ ልካቸውንም በአንድ ፓርቲ ኢህአዴግ እንደሚመሩ የሚያስቡም ሰዎች ናቸው፡፡ የሚሰጋው አካል ከፈለገ ተፎካካሪ ፓርቲ አደራጅቶ ለምን ኢህአዴግን ከስልጣን አውርዶ ሀገሪቱን አያስተዳድሩም ሲሉም ተናግረዋል፡፡