አባይ ሚዲያ ዜና- ጥቅምት 23፣2012

ትውልደ ኢትዮጵያውያን በሁሉም የአገሪቱ የፋይናንስ ተቋማት ውስጥ መዋዕለ ንዋያቸውን ማፍሰስ የሚያስችላቸውና የፋይናንስ ተቋማትም ተፈጻሚ የሚያደርጉት አዲስ ረቂቅ መመርያ፣ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መዘጋጀቱ ተገለጸ፡፡

ብሔራዊ ባንክ ሁሉም የአገሪቱ የፋይናንስ ተቋማት አስተያየት እንዲሰጡበት የላከው ይህ ረቂቅ መመርያ፣ ትውልደ ኢትዮጵያዊ የውጭ አገር ዜጎች ወይም በትውልደ ኢትዮጵያዊ ባለሀብቶች የሚተዳደሩ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ድርጅቶች፣ በፋይናንስ ተቋማት ውስጥ የአክሲዮን ባለድርሻ ለመሆን የሚያስችላቸውን ዝርዝር ሕግጋቶች የያዘ ነው፡፡

ረቂቅ መመርያው ትውልደ ኢትዮጵያውያን በሁሉም የፋይናንስ ተቋማት እንዴት መዋዕለ ንዋያቸውን ማፍሰስ እንዳለባቸው ከመጠቆሙም በላይ፣ የፋይናንስ ተቋማት አክሲዮኖቻቸውን ሲሸጡ ማድረግ አለባቸው የተባሉ ተግባራትንም ያካተተ ነው፡፡

የፋይናንስ ተቋማት አክሲዮኖች ሽያጭ ዝግጅትም ሆነ ተያያዥ የባለአክሲዮኖች ምዝገባ በኢትዮጵያ ውስጥ በሕግ አግባብ ብቻ መፈጸም እንደሚኖርበትም ይኸው ረቂቅ ያመለክታል፡፡