አባይ ሚዲያ ዜና- ጥቅምት 24፣2012

በኢትዮጵያ የብሄርም ሆነ የሀይማኖት ግጭት የሚቀሰቅሱ አካላትን በአለምአቀፉ ፍርድቤት መጠየቅ እንደሚቻል የህግ ምሁራን ተናግረዋል፡፡

የሕግ ባለሙያና የሰብዓዊ መብት ተከራካሪ አቶ አለልኝ ምሕረቱ ‹‹የጅምላ ግጭት፣ ግድያና ማኅበረሰብ የማይለይ ጥፋት ሲፈጸም ‹ያገባኛል› ያለ ሰው ሁሉ በቡድንም ይሁን በግል ጥፋተኞቹን ወደ ሕግ ማቅረብ ይገባዋል፤ በዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት ጭምር መክሰስ ይቻላል›› ይላሉ፡፡

በኢትዮጵያ በርካታ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች እንዳሉ የተናገሩት አቶ አለልኝ የተመዘገቡና ሕጋዊ ፈቃድ ያላቸው የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ማንነትንና ሃይኖማትን መሠረት አድርገው ግጭት የሚቀሰቅሱና ጥፋት ያደረሱ ሰዎችን መክሰስ እንደሚችሉም ተናግረዋል፡፡

ባለሙያው የሰብዓዊ መብት ድርጅታቸው እንቅስቃሴዎችን እንደጀመረ በመግለጽ በግለሰብ ደረጃም ቢሆን በማኅበረሰብ ላይ የሚደርስን ጥቃት ለማስቆም፣ ካሳ ለማስካስ እና ጥፋተኞችን ወደ ሕግ እንዲቀርቡ ማድረግ እንደሚቻልም አመላክተዋል፡፡

‹‹ነገር ግን በወንጀል ለመጠየቅ ዓለማቀፋዊ ሕጎች የሚፈቅዱ ቢሆንም ሁሉም ሰው ችግሩ የራሱን ቤት እስኪያንኳኳ ስለሚጠብቅ በቶሎ እልባት እንዳያገኝ ሆኗል›› ነው ያሉት የሕግ ባለሙያና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ፡፡

የሚሠሩበት የሰብዓዊ መብት ድርጅት አባላት ከተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች የተውጣጡ እንደሆኑ የገለጹት አቶ አለልኝ የገንዘብ ችግር እንዲህ ዓይነት ችግሮችን ለመሟገት እንቅፋት እንደሆነባቸውም አስታውቀዋል፡፡

“የሕግ የበላይነት በሀገሪቱ የለም” ያሉት አቶ አለልኝ ‹‹መንግሥት የሕግ የበላይነትን ለማስከበር አቅም አጥቷል፤ አቅም አላነሰኝም ካለ ደግሞ የኢትዮጵያን መበጣበጥ ይፈልጋል ማለት ነው›› ሲሉም በመንግሥት በኩል ያለውን ግራ አጋቢ ሂደት ገልጸዋል፡፡

የመንግሥት ተቀዳሚ ተግባር የዜጎችን ደኅንነት መጠበቅ መሆኑን ያመለከቱት የሕግ ባለሙያውና የሰብዓዊ መብት ተከራካሪው የዜጎችን ደኅንነት ማስጠበቅ ያልቻለ መንግሥት ስልጣን መያዝ እንደማይገባውም ተናግረዋል፡፡