አባይ ሚዲያ ዜና- ጥቅምት 24፣2012

ከሰሞኑ በኦሮሚያ፣ በሀረርና በድሬ ዳዋ በነበሩት ግጭቶችና ግድያዎች ዙሪያ ጠቅላይ ሚንስትሩ የሰጡት መግለጫ የማኅበራዊ ትስስር ገፆች አጀንዳ ሆኗል፡፡

እሁድ ጥቅምት 23 ለተወሰኑ የመገናኛ ብዙኃን ብቻ በተሰጠው መግለጫ ጠቅላይ ሚንስትሩ የሟቾችን ማንነት በብሔርና እምነት ከፋፍለው ይፋ ያደረጉ ሲሆን በርካቶች መንግሥት በግድያው ላይ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ተሳትፎ ያላቸው ወንጀለኞች ላይ ትኩረት ማድረግ ሲገባው የሟቾችን ማንነት መዘርዘሩ ምን ፋይዳ አለው ሲሉ ቁጣና ቅሬታቸውን በማኅበራዊ ትስስር ገጾች እያሰሙ ነው፡፡

ጠቅላይ ሚንስትሩ በሹመታቸው ወቅት ‹‹ስንኖር ኢትዮጵያዊ ስንሞት ደግሞ ኢትዮጵያ እንሆናለን›› ያሉትን በማስታወስም፤ ቃሉ የት ተረስቶ ነው ዛሬ የሟቾች ማንነት ላይ የሚተኮረው የሚለው ጥያቄ ከብዙዎች እየተነሳ ነው፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትሩ መግለጫ ላይ አስተያየታቸውን ለአባይ ሚዲያ የገለጹት የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ አብን ሊቀመንበር ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ ዶ/ር አቢይ በመግለጫቸው ሞተዋል ካሏቸው የአማራ ተወላጆች ቁጥር አብን የደረሰው የሟቾች ቁጥር እንደሚበልጥ የተናገሩ ሲሆን የሟቾችን ብሄር መጥቀሱ ለምን እንደተፈለገ አልገባኝም ብለዋል፡፡

ዶ/ር ደሳለኝ አክለውም የሟቾች ቁጥር ትልቁ ጉዳይ ሆኖ መነሳቱ አግባብነት የለውም ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ የሟቾችን ማንነት በብሔርና በእምነት ለይቶ ማቅረብ ያስፈለገበትን ምክንያት ሲያስረዱ ‹‹አንድ ችግር ሲያጋጥም የማይገድለው ብሔር፣ ፆታና እምንት ›› እንደሌለ ለማሳየት ነው ብለዋል፡፡

ይህ ዓይነቱ መግለጫ ቁርሾን የበለጠ አያጋግልም ወይ የሚለው ስጋትም አብሮ እየተነሳ ሲሆን፣ መንግሥት አሁንም ወንጀለኞችን ለፍርድ ያቅርብ የሚለው ጥያቄ አሁንም በርትቶ ቀጥሏል፡፡