አባይ ሚዲያ ዜና- ጥቅምት 25፣2012

ሕብረቱ “በማራቶን ደጋግመን ያሸነፍነውን ያህል፣ ሰሞኑን በጭካኔ ሬከርድ ሰብረናል!” በሚል ርዕስ ሰሞኑን በኦሮሚያ ክልል ተከስቶ ከ80 በላይ የሆኑ ንጹሃን ዜጎችን በአሰቃቂ ሁኔታ የቀጠፈውን ክስተት አስመልክቶ መግለጫ አውጥቷል።

ሕብረቱ ለኢትዮ 360 በላከው መግለጫ ኢትዮጵያ ሃገራችን ፈታኝ ወቅት ላይ ትገኛለች ያለ ሲሆን ሕወሃትን ለማውረድ ብዙ መስዋእትነት የተከፈለበት ለውጥም በመቀልበስ ላይ መሆኑ ሃሜት ሳይሆን ሃቅ ነው ብሏል ሕብረቱ በመግለጫው።

መግለጫው ጥቃት አድራሾች ግድያ የፈጸሙት “ነፍጠኛ” ከሚሉት የአማራ ወገን ብቻ ሳይሆን የጋሞ፣ የጉራጌ እና የዶርዜ ማህበረሰብ እንዲሁም ሙስሊምም ክርስቲያንም ይገኙበታል ሲል ያስቀምጣል።

በተጨማሪም ቤተክርስቲያንና መስጊድ፣ የመኖሪያ ቤቶች እና የንግድ ተቋማት መቃጠላቸውንም መግለጫው ያትታል።

ትናንት በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የሰላም የኖቤል ሽልማት ማሸነፍ አገራችን በዓለም ጋዜጦች በአድናቆት ሲዘገብላት እኛ ኢትዮያውያኖች በያለንበት አንገታችንን ቀና አድርገን የነበርነውን ያህል ሰሞኑን በተከሰተው ጭካኔ ደግሞ አንገታችንን እንድንደፋ ተደርገናል ሲል ህብረቱ ይናገራል።

ሰፊው የኦሮሞ ሕዝብም በቀየው በተከሰተው ኢ-ሰብአዊ ድርጊት ከሌላው ወገኑ ጋር እንደተሸማቀቀና በእጅጉ እንዳዘነ የሚያከራክር ጉዳይ አይደለም ያለው ህብረቱ አንድ መረሳት የሌበትና ሊሰመርበት የሚገባ ጉዳይ ቢኖር የኢትዮጵያ ሕዝብ ትናንት የልጆቹን ደም ገብሮ ሕወሃትን ያስወገደው የባሰ ዘመን ለማስተናገድ አይደለም ብሏል።

ሕብረቱ አሁንም ቢሆን ሕዝብን በማበጣበጥ ሕግ የሚጥሱትን መንግሥት ፈጥኖ በመያዝ ሕጋዊ እርምጃ እንዲወሰድባቸው ካላደረገ የዜጎቹን ክብርና እምነት ያጣል ሲል በመግለጫው አብራርቷል።

ሕዝብ ለመንግሥት ሃላፊነት የሰጠው ከሁሉም በላይ የሕግን የበላይነት እዲያስከብርለት ነው ያለ ሲሆን ስለዚህ አጥፌዎች ያላቸው ጡንቻ ተፈርቶ ፍትህ መዘግየትና መጓደል የለባትም ሲል አሳስቧል የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ንቅናቄ ሕብረት ።