አባይ ሚዲያ ዜና- ጥቅምት 25፣2012

ለጉሙሩክ ደረቅ የመቅረጫ ጣቢያ ግንባታ ይፈለጋል የተባለው ቦታ ለ20 ዓመት ወደ ሥራ ባለመግባቱ በከተማው እድገት ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩን ነዋሪዎች የተናገሩ ሲሆን የምዕራብ ጎንደር ዞን ንግድ፣ ኢንዱስትሪ እና ከተማ ልማት መምሪያ ደግሞ ችግሩ የኢትዮጵያ ጉሙሩክ ኮሚሽን መሆኑን ገልጿል፡፡

የመተማ ዮሐንስ ነዋሪዎች እንደገለጹት መንግሥት ከኢትዮጵያና ሱዳን ድንበር በመነሳት በተለምዶ ገብርኤል እየተባለ እስከሚጠራው አካባቢ የሚገኘውን አንድ ኪሎ ሜትር የሚጠጋ ቦታ ከ1991 ጀምሮ ለልማት ጠይቆ ነበር፡፡

በዚህም ምክንያት ለመቅረጫ ጣቢያ ግንባታ ይፈለጋል የተባለው ቦታ ለ20 አመት ፕላን ሳይሰራለት ቆይቷል፡፡

ማኅበረሰቡም ለታለመለት ዓላማ ይውላል በሚል አካባቢውን ማልማት የሚያስችል አቅም እያለው ያለምንም ልማት እንዲኖር ተደርጓል ብለዋል፡፡

“ማስተር ፕላኑ” ተግባራዊ ባለመደረጉ የውኃ፣ መብራት፣ መንገድ እና ሌሎችም መሠረተ ልማቶች ለማሟላት እና ወደ ግንባታ ለመግባት እንዳስቸገራቸው ነው ነዋሪዎቹ የተናገሩት፡፡

የምዕራብ ጎንደር ዞን ንግድ፣ ኢንዱስትሪ እና ከተማ ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ ሆነዓለም አሻግሬ እንደተናገሩት ለጉሙሩክ ደረቅ ጣቢያ ግንባታ የተጠየቀው ቦታ ተግባራዊ ባለማደርጉ በከተማው እድገት ላይ ተጽዕኖ አሳድሯል፡፡
ለበርካታ ዓመታት ነዋሪው እንዳያለማ ተደርጎ ከቆየ በኋላ ተቋሙ ግምቱን መክፈል እንደማይችል እና 10 ሄክታር መሬት ግምት ተሰርቶ እንዲቀርብለት ኮሚሽኑ እንደጠየቀ አቶ ሆነዓለም ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ጉሙሩክ ኮሚሽን ፕሮጀክት መሀንዲስ ኢንጅነር ጌታሁን አባተ በበኩላቸው እንደገለጹት ደግሞ ለመገንባት የታቀደው “የደረቅ ወደብ” ግንባታ የኮሚሽኑ ተግባር እና ኃላፊነት ባለመሆኑ ለፕሮጀክቱ መጓተት ምክንያት ሆኗል፡፡

ችግሩንም ለመፍታት በኮሚሽኑ ስልጣን ሊገነባ የሚችል እና የተለያዩ አገልግሎት ሰጭ ተቋማት በአንድ ቦታ ላይ አገልግሎት ሊሰጡ የሚችሉበት መቆጣጠሪያ ጣቢያ ለመገንባት 1 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ቦታ ተጠይቋል፡፡