አባይ ሚዲያ ዜና- ጥቅምት 25፣2012

በየተቋማቱ ያሉ ቅሬታ ሰሚዎችና የስነ ምግባር መኮንኖች የተጣለባቸውን ኃላፊነት በአግባቡ እየተወጡ እንዳልሆነ የፌዴራል ስነ ምግባርና ጸረሙስና ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

የጸረሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር አየልኝ ሙሉዓለም እንደተናገሩት፣ በየተቋማቱ ያሉ ቅሬታ ሰሚዎችም ሆኑ የስነምግባር መኮንኖች የመስሪያ ቤቶቹ የበላይ ኃላፊዎች አማካሪ ከመሆን ባለፈ ምንም ዓይነት የወሳኝነት ሚና የላቸውም፡፡

አንዳንድ ጊዜ አለፍ ብለው ጉዳዮችን ለማጣራት የሚያደርጓት ትንሿ ጥረታቸው እንኳን ‹‹በማያገባችሁ ገባችሁ›› በሚል እርምጃ ታስወስድባቸዋለች፡፡

እንደኮሚሽነሩ ገለጻ፣ ተቋማት ለስራው የሚመድቧቸው ሰዎች ትልቅ ኃላፊነት ለመውሰድ ቁርጠኛ ያልሆኑ፣ ይህንን አደጋ ያለውን ስራ ተከታትለውና በተለያየ መንገድ መርምረው ተጠያቂ ለማድረግ የሚያስችል አቅምና ፍላጎት የላቸውም፡፡

‹‹አንዳንድ ጊዜ በስራ ደከም ያሉ ሰራተኞችን ‹ቦታ ተሰጥቶታል› ለማለት ብቻ ወደዚህ የስራ ክፍል የመመደብ ሁኔታ ይታያል›› ያሉት ኮሚሽነሩ፣ ይህ መሆኑ ደግሞ ሰዎቹ በስራቸው ውጤታማ እንዳይሆኑና የጸረ ሙስና ትግሉም ፍሬ እንዳያፈራ እንዳደረገው ገልፀዋል፡፡

‹‹ተቋማት ሙስናን ለመከላከል ለስራው የሰጡት ትኩረት እጅግ አናሳ ነው፤ አንዳንዶች ደግሞ ይህን ኃላፊነት የሌላ አካል ስራ አድርገው እስከማየት ይደርሳሉ፤ ኮሚሽኑ ስብሰባ ሲጠራ በቀጥታ የሚመለከታቸውን ሰዎች አለመላካቸው ለዚህ ማሳያ ነው›› ብለዋል፡፡

‹‹ይህ ሁኔታ በዚህ መቀጠል የለበትም›› ያሉት ከሚሽነሩ፣ ተቋማት በተቻለ መጠን ለስራው ትኩረት በመስጠት ለዘርፉ ትክክለኛውን ሰው በመመደብ የስነ ምግባር መኮንኖች ከአማካሪነት የዘለለ ስራ እንዲሰሩ እድሉን መስጠትና ሁኔታዎችን ማመቻቸት እንደሚገባቸው ተናግረዋል፡፡