አባይ ሚዲያ ዜና-ጥቅምት 25፣2012

የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ሀላፊ ዶክተር ሰሎሞን አሰፋ ለአባይ ሚዲያ እንደተናገሩት ባለፈው ሰኔ ወር ከሳዑዲ አረቢያ ወደ አፋር እና ሶማሌ ክልሎች እንደገባ የሚነገረው የበረሀ አንበጣ መንጋ ወደ አማራ ክልል እንዳይገባ የመከላከል ስራ ሲሰራ ቢቆይም የመራባት አቅሙ ከፍተኛ በመሆኑና የፌደራል መንግስት ያደረገው የመከላከል ዘመቻ ዝቅተኛ በመሆኑ የአንበጣ መንጋ ወደ ክልሉ ሊገባ ችሏል፡፡

የአንበጣ መንጋው ክልሉን ከአፋር እና ሶማሌ በሚያዋስኑ  በሰሜን ወሎ ፣ደቡብ ወሎ እና በኦሮሞ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞኖች የተከሰተ ሲሆን በመከላከል ዘመቻው ተማሪዎች፣የመንግስት መስሪያ ቤቶች እና የአካባቢው ነዋሪዎች ከፍተኛ ርብርብ እያረጉ ቢሆንም በቂ እንዳልሆነና የፌደራል መንግስት አውሮፕላኖችን በመጠቀም የጸረ ነፍሳት ርጭት ሊያደርግ እንደሚገባ ዶክተር ሰሎሞን ገልጸዋል፡፡

የመራባት አቅሙ እና የበረራ ፍጥነቱ ከፍተኛ በመሆኑ የበረሀ አንበጣው በአጭሩ ካልተገታ የሀገሪቱን የሰብል ምርት በከፍተኛ ሁኔታ አደጋ ውስጥ ይከተዋል ብለዋል፡፡

የአንበጣ መንጋው ኢትዮጵያ ውስጥ በአፋር፣ሶማሌ፣አማራ፣ኦሮሚያ እና ትግራይ ክልሎች የተከሰተ መሆኑ ይታወቃል፡፡