አባይ ሚዲያ ዜና-ጥቅምት 26፣2012

የአማራ ዴሞክራሲያዊ ሃይል ንቅናቄ አዴሃን ሊቀመንበር አቶ ተስፋሁን አለምነህ ከትላንት በስትያ ብርጋዲየር ጄነራል ከማል ገልቹ ከወጣት ተማሪዎች ጋር በመሆን በአኖሌ ሀውልት በተገኙበት ወቅት ያደረጉት ንግግር እታገልለታለሁ ለሚሉት የኦሮሞ ህዝብም ሆነ ለሌላው ማህበረሰብ የማይጠቅምና ፍጹም ተቀባይነት የለውም ሲሉ ኮንነዋል፡፡

አቶ ተስፋሁን ብ/ጄ ከማል ገልቹ የተገኙበት ቦታ የውሸት ትርክት የተፈጠረበት በመሆኑ ያስተላለፉትን መልዕክት ከቀልባቸው ሆነው እንደገና ቢመዝኑት መልካም ነው ሲሉ ለአባይ ሚዲያ ተናግረዋል፡፡

ብ/ጄ ከማል በንግግራቸው ላይ ኦዲፒ ከነፍጠኛ ጋር አብሮ እየሰራ ነው ማለታቸው የተሳሳተ እንደሆነ የሚገልጹት አቶ ተስፋሁን እንደ ፓርቲ ህወሃት በስልጣን ዘመኑ የትግራይ ህዝብን እንዳልጠቀመው ሁሉ ገዢው ኦዲፒ ኢህአዴግም የኦሮሞ ህዝብን እያገለገለ አይደለም ከማለት ባለፈ ከነፍጠኛ ጋር ማገናኘቱ አስፈላጊ አይደለም ብለዋል፡፡