ንጉስ ሚካኤል ፊታውራሪ ዲነግዴና ዶር አብይ አህመድ( በፋሲል የኔአለም)

ለዚህ ጽሁፍ መነሻ የሆነኝ ዶር ዳኛቸው አሰፋ ማኪያቬሊ፣ ሊጋባው በየነና ዶ/ር አብይ አህመድ በሚል ርዕስ ያቀረቡት ንግግር ነው። የንግግሩ መልዕክት ባጭሩ ዶ/ር አብይ አህመድ በአዳዲስ “ሊጋባዎች” ላይ ቆራጥ እርምጃ ወስደው አገሪቱንም ስልጣናቸውንም ያድኑ የሚል ነው። “በስልጣን ላይ እያሉ ሰው አስገርፈው አስገድለዋል” በሚል በአንድ ተራ ዜጋ ተከሰው ደጃች ተፈሪ መኮንን ፊት ቀርበው ከስልጣናቸው የተሻሩት ደጃዝማች በየነ ወንድማገኘሁ፣ እንደገና በአልጋ ወራሹ ላይ አድማ ለማስነሳት አሲረዋል በሚል ተከሰው ፍርድ ቤት በቀረቡበት ወቅት፣ ችሎት ላይ እያሉ አልጋወራሹን በመናገራቸው ከ 20 በላይ ጅራፍ ተገርፈው ወደ ግዞት እንደተላኩ ተጽፎ ይገኛል። ሊጋባው በየነ ጣሊያን ኢትዮጵያን ስትወር “አገር ከፖለቲካ በላይ ነው” በማለት ወደ ማይጨው ዘመተው በጀግንነት ተሰውተዋል። ከሊጋባው በየነ ግርፋት በሁዋላ ሸዋ ለጥ ብሎ እንደተገዛ በዶር ዳኛቸው የተሰጠው አስተያየት በማስረጃ የሚደገፍ አይመስለኝም። ያም ሆነ ይህ ግን በተገቢው ጊዜና ቦታ ላይ ተመጣጣኝ የሃይል እርምጃ መውሰድ ለአንድ የአገር መሪ አስፈላጊ መሆኑን የማኪያቬሊን ምክር ጠቅሰው የሰጡት አስተያየት ትክክል ነው ብዬ እቀበላለሁ። ነገር ግን ማኪያቬሊም ቢሆን፣ የሃይል እርምጃ የሚወሰድበትን ትክክለኛ ጊዜና ቦታ የሚናገር ባለመሆኑ፣ ለዶር አብይ የቀረበው የማኪያቬሊ ምክር ሙሉ ነው ብሎ መናገር አይችልም። ከሊጋባ በየነ ታሪክ ይልቅ የወሎ ገዢ በነበሩት በንጉስ ሚካኤልና በ ፊታውራሪ ሃብተጊዮርጊስ ዲነግዲ ( አባ መላ) መካከል የነበረ አንድ የጦርነት ክስተት የዶ/ር አብይን አጣብቂኝ ብቻ ሳይሆን፣ የሃይል እርምጃ መቼ መወሰድ እንዳለበት የሚያመላክት ይመስለኛል።

ልጃቸውን፣ ልጅ እያሱን፣ የሸዋ መኳንንት አድመው ከስልጣን እንዳወረዱዋቸው የሰሙት ንጉስ ሚካኤል፣ በጣም ተበሳጭተው መኳንንቱን ለመውጋትና የልጃቸውን ዙፋን ለማስመለስ አሰቡ። የሸዋ መኳንንት በአዲስ አበባ የተጠናከረ ጦር ስላልነበራቸው፣ ንጉስ ሚካኤል በፍጥነት መጥተው ያጠፉን ይሆን ብለው ፈሩ። ከሳምንታት በሁዋላ ንጉስ ሚካኤል ከ 60 ሺ በላይ የሚሆን ጦር አስከትተው ከደሴ ወደ ሸዋ ዘመቱ። ሸዋን ጭንቅ ገባው። ተፈሪ መኮንንም ግምጃ ቤት ያለውን ጠመንጃ ሁሉ ለአዲስ አበባ ሰው አከፋፍለው “ራስህን ተከላከል” አሉት። የጦሩ ሚኒስትር ፊታውራሪ ሃብተጊዮርጊስ ዲነግዴ ( አባ መላ) ንጉስ ሚካኤል አዲስ አበባ ሳይደርሱ ለመከላከል እንዲያመች ብለው ጥቂት ጦራቸውን ይዘው ወደ ቅምብቢት ወረዱ። አዲስ አበባ ወደሚገኙት ወደ ደጃች ተፈሪ መኮንን እየጮኹ ጦር በቶሎ እንዲላክላቸው ቢያሳስቡም የሸዋ ጦር ገና ስላልተሰባሰበ የሚሳካ አለሆነም። በዚህ ላይ እያሉ ዲነግዴ ጊዜ ለመግዛት እንዲያመቻቸው ለንጉስ ሚካኤል ደብዳቤ ጻፉ። የደብዳቤውም ይዘት “ንጉስ ሆይ ሁሉም የእርስዎ ነው። እንዴት እኛ እርስ በርሳችን እንዋጋለን፣ እኔም ከግብረ አበሮቼ ጋር እርስዎ ያሉበት ድረስ እመጣለሁና የደሃ ደም በከንቱ እንዳይፈስ ዘመቻውን ይተውት።” የሚል ይዘት ነበረው። ንጉስ ሚካኤል በጣም ሩህሩህና ደግ ስለነበሩ፣ “ሃብተጊዮርጊስ እውነቱን ነው ፣ ለምን የደሃ ደም በከንቱ ይፍሰስ፣ ሃብተጊዮርጊስ ወደኛ ከገባ ማን ይዋጋናል” ብለው የአማካሪዎቻችውን ምክር ባለመስማት ጦራቸውን እርምጃ ከመውሰድ አዘገዩት። በእያገሩ የተበታተነው የሽዋ ጦር አዲስ አበባ እንደደረሰ ወደያውኑ ወደ ሰገሌ ዘመተ። የዋሁ ንጉስ ሚካኤል፣ ሃብተጊዮርጊስ በተባለው ቀን ይመጣሉ ብለው ድንኳን አዘርገተው እና ድግስ አዘጋጅተው ቢጠብቁ አባ መላ የውሃ ሽታ ሆነው ቀሩ። ንጉሱ መታለላቸውን ካወቁ በሁዋላ፣ ዲነግዴን ተራ ስድብ ሰድበው ማርከው ለመቅጣት ጦራቸውን ግፋ በለው አሉ። ግን አልሆነም፤ በቀላሉ ማገኘት ይችሉት የነበረውን ድል በመታለላቸው ከእጃቸው ላይ ጣሉትና ግዞተኛ ሆነው ህይወታቸው አለፈ።

የሁለቱ ሰዎች ታሪክ አንድ እርምጃ መቼ መወሰድ እንዳለበትና እንደሌለበት በደንብ የሚያሳይ ነው። ንጉስ ሚካኤል ባይታለሉና የዲነግዴ ጦር ሳይጠናከር እርምጃ ቢወስዱ ኖሮ፣ አሸናፊ ሆነው የልጅ እያሱንም ይራሳቸውንም ዙፋን ያስጠብቁ ነበር። ፊታውራሪ ሃብተጊዮርጊስም በድንፋታና በስሜት ሃይላቸውን ሳይጠናከሩ በያዙት ጦር ብቻ የንጉስ ሚካኤልን ጦር እገጥማለሁ ቢሉ በቀላሉ ተሸንፈው አወዳደቃቸው የከፋ ይሆን ነበር።

እዚህ ላይ ሃይለስላሴ የማኪያቬሌን ምክር ተግባራዊ ያደርጉበትን አንድ ድርጊት ላንሳ። የአጼ ሃይለስላሴ ባለቤት እቴጌ መነን የንጉስ ሚካኤል የልጅ ልጅ የልጅ እያሱ ደግሞ አክስት ናቸው። መርስዔ ሃዘን ወልደ ቂርቆስ እንደነገሩን ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊት ደጃዝማች ተፈሪ መኮንን ባለቤታቸውንና እና የባለቤታቸውን እናት ወ/ሮ ስሂን ሚካኤልን ለአያታቸው ወይም ለአባታቸው አድልተው የጦር መረጃ ያቀብሉ ይሆናል በሚል ስጋት በአንድ ክፍል ውስጥ አግተዋቸው ( አስረዋቸው) ነበር። እንግዲህ እቴጌ መነን ከባላቸው ይልቅ ለአያታቸው፣ ወ/ሮ ስሂን ደግሞ ከአማቻቸው ይልቅ ለአባታቸው እና ለወንድማቸው እያሱ አድልተው መረጃ ያቀብላሉ ተብለው ከታሰሩ ማኪያቬሊ ከተፈሪ ጓሮ ቤት ቀልሰው ያማክሩ እንደነበር እናያለን። ተፈሪ የማኪያቬሊን ምክር ተግባራዊ ባያደርጉና በይሉኝታና ስለፍቅር ሲሉ ሚስታቸውንና አማታቸውን ባያስሩ ኖሮ፣ ማን ያውቃል፣ ንጉስ ላይሆኑም ይችሉ ነበር።

ዶ/ር አብይ አህመድ በንጉስ ሚካኤልና በዲነግዴ መሃል የቆሙ ይመስለኛል። የትና መቼ እንደምትጠቀምበት ካላወቅህ፣ ሃይል ብቻውን ዋጋ የለውም ይባላል። ብዙዎች ደግሞ በየትኛውም መንገድ ቢሆን እርምጃ እንዲወስድላቸው ይወተውታሉ ። ከእርምጃ በፊት የዲነግዴ እና የንጉስ ሚካኤል አይነት የቼዝ ጨዋታ መኖሩ ብዙ አያስጨንቃቸውም፤ ብቻ የቀድሞ የቻይና መሪ ዴንግ ዚዮፒንግ በአንድ ወቅት ተናገሩ እንደሚባለው ድመቱ ቀለሙ ምንም ይሁን ምን አይጥ ይዞ እንዲያሳያቸው ይፈልጋሉ። “It doesn’t matter whether the cat is black or white as long as it catches mice.”ብዙዎች ስለ ድመቱ ቀለም ወይም ውበት መስማት እያንገሸገሻቸው እንደመጣ የምንታዘበውም አይጥ ይዞ ሊያሳያቸው ስላልቻለ ነው። አንዳንዶች ድመቱ አይጥ መያዝ ካልቻለ፣ ወጥመድ ገዝተን ቤታችንን ከአይጥ እንከላከላለን ሲሉ የሚሰሙትም ለዚህ ነው። ድመቱ ደግሞ ” የአደኑን ስራ ለእኔ ተውት” እያለ ነው። ማን ትክክል እንደሆነ የሚታወቀው ከውጤት በሁዋላ እንጅ ከውጤት በፊት አለመሆኑ ለመፍረድ ያስቸግራል። ፈረንጆች The proof of the pudding is in the eating እንደሚሉት ነው። ለማንኛውም በአንድን ፈልሳፋ ምክር ጽሁፌን ልቋጭ። Failure comes from resisting that which works best …in favour of some systemic method or principle claiming universal validity. ግርድፍ ተርጉም ፦ ለውጤት የሚያበቃህን ዘዴ የምታውቀው አንተ ነህ ነገር ግን የሆነ አስራር ወይም የሆነ አለማቀፍ መርህ ለመከተል ስትል ብቻ በትክክለኛው ጊዜ መውሰድ ያለብህን ወሳኝ እርምጃ ሳትወስድ ከቀረህ ሽንፈት ይከተልሃል።”